የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሲዳማ ክልል የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን እና የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር አከናወነ

ነሃሴ1/2013(ዋልታ) – የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሲዳማ ክልል የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን እና የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርን በማከናወን ላይ ይገኛል።

ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መሰረት በክልሉ አለታ ወንዶ ከተማ የስድስት አቅመ ደካማ እማወራዎችን እና አባወራዎችን ቤት አፍርሶ የመገንባት ስራን የሚያከናውን ሲሆን በአረንጓዴ  አሻራ መርሀ ግብር አስር ሺ ችግኞችን በአለታ ወንዶ ወረዳ ቲቲራ ቀበሌ ለመትከል ታቅዷል።

በመርሀ ግብሩ ላይ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶር ሊያ ታደሠን ጨምሮ ከ70 በላይ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሠራተኞች ተሳትፈዋል።

እንደ ሀገር የተጀመረው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እና የአረንጓዴ አሻራ ስራ አንድነትን እና ፍቅራችንን የሚያጠናክር እና እንደሀገር ከተባበርን የማንሻገረው ችግር አለመኖሩን የሚያሳይ ነው ያሉት ዶር ሊያ ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ በመላው ሀገሪቱ የዚህ አካል በመሆኑ ደስተኛ ነው ብለዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እስካሁን በተጀመረው ኢትዮጵያን የማልበስ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ከ800ሺ በላይ ችግኞችን መትከሉም ተገልጿል።

የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ሰላማዊት መንገሻ በበኩላቸው ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በክልሉ የተጀመረውን የክረምት በጎ ፈቃድ ስራዎችን ለማገዝ በመገኘቱ አመስግነው ክልሉ ከመደበኛው የጤና ስራ ጎን ለጎን ለሚያከናውናቸው ማህበረሰብ ተኮር በጎ ፈቃድ እና አከባቢ ጥበቃ ስራዎች አቅምን የሚጨምር ነው ብለዋል። በቀጣይም ክልሉ የተጀመሩ ስራዎችን በማስቀጠል ለውጤታማነቱ ይተጋልም ብለዋል።

የአለታ ወንዶ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እየሠጠ ያለውን አገልግሎት እና ነባራዊ ሁኔታን የጤና ሚኒስቴር አመራሮች እና ሠራተኞች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

(በድልአብ ለማ)