የካቲት 09፣ 2013 (ዋልታ) – የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣው አዋጅ ተፈጻሚ መሆን እንዳልጀመረ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከብሮድካስት ባለስልጣን ጋር በመሆን የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ፣ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣው አዋጅ እንዲሁም የዜና አገልግሎት ዓለም አቀፍ ፋይዳና ተሞክሮ በሚል የተዘጋጀ የውይይት መድረክ ትናንት በአዳማ ተካሄዷል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየካቲት 2012 ዓ.ም የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ማፅደቁ ይታወሳል።
ይሁንና አዋጁ እስካሁን ተፈጻሚ ሲሆን አልታየም፣ በአዋጁ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን የሚጥሱ ድርጊቶች እየተፈጸሙ እርምጃ እየተወሰደ አይደለም፣ ወደ ፍርድ ቤትም ጉዳዮች እየመጡ አይደለም ? የሚሉ ጥያቄዎች በውይይቱ ተሳታፊዎች ተነስተዋል።
የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የሕግ ጥናት ማርቀቅና ማጠቃለል ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ በላይሁን ይርጋ የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣው አዋጅ እስካሁን ተፈጻሚ ያልሆነው በቅድሚያ ስለ አዋጁ ግንዛቤ መፍጠር በማስፈለጉ ነው ብለዋል።
በአዋጁ ዙሪያ የግንዛቤና የስርጸት ስራ ሊጀመር በታሰበበት ጊዜ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመከሰቱ ግንዘቤ የመፍጠር ስራው ሊሳካ አለመቻሉን አስረድተዋል።
በክልሎች በአዋጁ የሕግ ጥሰት የተፈጸመባቸውን ጉዳዮች የመመርመርና አንዳንዶቹን ወደ ፍርድ ቤት የመውሰድ ሁኔታ ቢኖርም ቅድሚያ ማስተማር አስፈላጊ በመሆኑ ጉዳዮቹ እንዲያዙ መደረጋቸውንና የግንዛቤ ስራዎችን በስፋት በማከናወን አዋጁ በፍጥነት ተፈጻሚ እንዲሆን እንደሚደረግ ነው አቶ በላይሁን ያስረዱት።
የጥላቻ ንግግር ትርጓሜ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችና ተግባራትን ከግምት ያስገባና አስፈላጊው ትርጓሜ ላይ ጥንቃቄ የተደረገበት በመሆኑ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ ተጽዕኖ እንደማያሳድር ተናግረዋል።
የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣው አዋጅ ‘የጸረ-ሽብር አዋጅን የተካ ነው’ የሚለው ሀሳብ ትክክል እንዳልሆነና አዋጁ በመናገር ነጻነት ላይ ገደብ እንዳልጣለም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ ሁለቱ አዋጆች መንግስት በተለያዩ መስኮች ባደረጋቸው ማሻሻያዎች ለመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት ያሳያሉ ብለዋል።
(ምንጭ፡- ኢዜአ)