የጥምቀት በዓል በሰላም ተከብሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል የተሰጠ መግለጫ

ጥር 9/2014 (ዋልታ) በሀገራችን በየዓመቱ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኒስኮ ካስመዘገበቻቸው የማይዳሰሱ ቅርሶች ውስጥ አንደኛው መሆኑ ይታወቃል፡፡
በዚህ የጥምቀት በዓል ላይ መላው የሀገራችን ህዝብ በተለይም የእምነቱ ተከታዮች እምነታቸውን በነፃነት በአደባባይ ወጥተው በጋራ የሚያከብሩበት፣ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን የበለጠ የሚያጠናክሩበት፣ መንፈሳዊ እሴቶቻቸውን የሚያዳብሩበት፣ ተቻችለውና ተከባብረው በጋራ መኖርን ለመላው አለም ህዝቦች በምሳሌነት የሚያሳዩበት ታላቅ በዓል ነው፡፡
የዘንድሮውን የጥምቀት በዓል ልዩ የሚያደርገው ከሀዲው፣ አሸባሪውና ተላላኪው የህወሃት ጁንታ ቡድን የሀገራችንን አንድነት ለመናድ የከፈተውን መጠነ ሰፊ የእብሪት ወረራ በድል አድራጊነት በተወጣንበት ማግስት የሚከበር እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የመሩትን “ዘመቻ ለህብረ-ብሄራዊ አንድነት” ውጤታማነት ተከትሎ ባደረጉት ጥሪ መሰረት ወደ ሀገራቸው የመጡ በርካታ የዲያስፖራ አባላትም የሚታደሙበት መሆኑ ነው።
በተመሳሳይ በዓሉ የቱሪስት መስህብ እንደመሆኑ መጠን በርካታ ቱሪስቶችም ከውጭ ሀገር ወደ ሀገራችን ገብተው በዓሉን ከኛ ጋር ለማክበር ቀኑን እየተጠባበቁ ይገኛሉ። በመሆኑም በዓሉ ከኛ አልፎ የዓለም ህዝብ በዓል በመሆኑ ምዕመናኑም ሆኑ እንግዶቹ ደህንነታቸው በተጠበቀ አኳሃን በዓሉን በሰላም አክብረው እንዲመለሱ በማድረግ የሀገራችንን መልካም ገፅታ በመገንባት ለዓለም ህብረተሰብ ተምሳሌት ሆነን የምንታይበት በዓል በመሆኑ ነው።
ስለሆነም በመላው ሀገራችን በታላቅ ድምቀት የሚከበረው የጥምቀት በዓል ያለ ምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲከበር የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ከወትሮው በተለየ መልኩ በቂ ዝግጅት በማድረግ ስምሪት ወስዶ ወደ ተግባር መግባቱን ገልጿል፡፡
የጋራ ግብረ-ኃይሉ መላውን ሰላም ወዳድ የሀገራችንን ህዝብ ከጎኑ በማሰለፍ የጥምቀት በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲከበር ለማድረግ በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች በርካታ የፀጥታ አካላት ማሰማራቱን ገልፆ በታቦታት ማደሪያ ስፍራዎችና በርካታ የበዓሉ ታዳሚዎች በሚገኙበት አካባቢ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
ከጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የደህንነት ስጋቶችን አስቀድሞ ለመከላከል በበዓሉ ሂደት ርችት መተኮስ ለፀረ-ሰላም ኃይሎች ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር በመሆኑ ፍፁም የተከለከለ መሆኑን የጋራ ግብረ-ኃይሉ አስታውቆ በዓሉ በሚከበርበት ስፍራም ከሚመለከተው አካል ፈቃድ የሌላቸው ግለሰቦች እና ተቋማት ድሮን ማብረር ወይንም ማንቀሳቀስ እንደማይችሉ፣ ምንም አይነት የጦር መሳሪያ፣ ተቀጣጣይም ሆነ ስለታማ ቁሳቁስ ይዞ መንቀሳቀስ የማይቻል እንደሆነና ለሁላችንም ደህንነት ሲባል ፍተሻ የሚደረግ መሆኑን የበዓሉ ታዳሚዎች ከወዲሁ ተረድተው ትብብር እንዲያደርጉም በጥብቅ አሳስቧል።
በሌላ በኩል ከህብረተሰቡ በተገኘው መረጃ መሰረት በዓሉ በሰላም እንዳይጠናቀቅ የተለያዩ የግል አጀንዳዎችን አንግበው የበዓሉን ድምቀትና ስነ-ስርዓት ለማወክ እንዲሁም ግጭት ለማስነሳትና ሌሎች አደጋዎችንም ለማድረስ የተዘጋጁ አንዳንድ ፀረ-ሰላም ኃይሎች እንዳሉ ተደርሶበታል፡፡
የህወሃት ጁንታ ቡድንና የሸኔ ርዝራዦች ይህንን እንደመልካም አጋጣሚ ሊጠቀሙበት ስለሚችሉ የጋራ ግብረ-ኃይሉ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ በተጠንቀቅ እንደሚገኝ አስታውቋል።
ስለሆነም የሰላሙ ባለቤት የሆነው መላው ህዝባችን ይህንን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባና አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት በፍጥነት ለጋራ ግብረ-ኃይሉ ጥቆማ ለመስጠት በስልክ ቁጥር +251115-52-63-03፣ +251115-52-40-77፣ +251115-54-36-78 እና +251115-54-36-81 እንዲሁም በ987፣ 991 እና 816 ነፃ የስልክ መስመሮች መጠቀምና በአካባቢው ላለ የፀጥታ ኃይል መረጃውን በአካል ማድረስ እንደሚችል አስታውቋል፡፡
በመጨረሻም ለእምነቱ ተከታዮችና ለጥምር የፀጥታ ኃይል አባላት በሙሉ እንኳን ለጥምቀት በዓል በሰላም አደረሳችሁ እያለ በዓሉ የሰላም፣ የጤና፣ የፍቅርና የብልፅግና እንዲሆንላችሁ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ከልብ ተመኝቷል።
መልካም በዓል
ጥር 9 ቀን 2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ