የጦርነት ነጋሪት የሚጎስሙ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

ኅዳር 11/2015 (ዋልታ) በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሠላም እንዳይሰፍን የጦርነት ነጋሪት የሚጎስሙ ፅንፈኛ ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አሳሰቡ።
የመከላከያ ሚኒስቴር በደቡብ አፍሪካ እና በኬንያ የተደረገውን የሠላም ስምምነት በስኬት አጠናቀው ለተመለሱ የልዑካን ቡድን አባላት የምስጋና እና የዕውቅና መርኃ ግብር አድርጎላቸዋል።
የልዑካን ቡድኑ የኢትዮጵያን አንድነትና ጥቅም ባስጠበቀ መንገድ የሠላም ንግግሩን አሳክቶ መመለሱን የገለፁት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ስምምነቱ ግቡን እንዲመታ አበክረው አንደሚሠሩም ተናግረዋል።
የሠላም ስምምነቱ የመከላከያ ሠራዊቱ ያስገኘው ድል መሆኑን አውስተው የተደረሰውን ስምምነት የሚያናጉና የጦርነት ነጋሪት የሚጎስሙ ኃይሎች መቼም አይሳካላቸውም ብለዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በበኩላቸው በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሠላም ለማምጣት ሲባል የልዑካን ቡድኑ አባላት ብስለት በተሞላበት መንገድ ስምምነት እንዲካሄድ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ሥር በደቡብ አፍሪካ እና በኬንያ የተደረሰውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ከሁለቱም ወገኖች በትኩረት እየተሠራ መሆኑ በመርኃ ግብሩ ላይ ተገልጿል።
በዚህ መርኃ ግብር ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላን ጨምሮ ጄኔራል መኮንኖች፣ ዲፕሎማቶችና ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች መገኘታቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ አመላክቷል።