የጨበራ ዝሆን ዳና ሎጅ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የጠበቀ የቱሪስት መስህብ ነው – ሚኒስትሩ ሐብታሙ ተገኝ


ታኅሣሥ 13/2016 (አዲስ ዋልታ) የጨበራ ዝሆን ዳና ሎጅ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የጠበቀ የቱሪስት መስህብ እንዲሆን ተደርጎ መገንባቱን የማዕድን ሚኒስትር ሐብታሙ ተገኝ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካል የሆነውን የጨበራ ዝሆን ዳና ሎጅን መርቀው ከፍተዋል።

የጨበራ ዝሆን ዳና ሎጅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሁለት ዓመት በፊት ካስጀመሯቸው ፕሮጀክቶች አንዱ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ በአሁኑ ወቅት ፓርኩ እጅግ ውብ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የጠበቀና የተሟላ የቱሪስት አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ መገንባቱን አመላክተዋል።

ፓርኩን በምስራቅ አፍሪካ ብሎም በአፍሪካ የቱሪስት መስህብ ለማድረግ ሲሰራ መቆየቱንም ገልፀዋል።

ፓርኩ ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ቀጥሎ ተጠቃሽ በሆነው የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክት አቅራቢያ መገንባቱንም ለቱሪስት መስህብነት የላቀ ያደርገዋል ብለዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በበኩላቸው ለአገልግሎት ክፍት የተደረጉት የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎች የተፈጥሮ ሚዛንን ከመጠበቅና ሰውና ተፈጥሮን ከማሰናሰል ባሻገር ኃብት ለመፍጠር ዕድል ሰጥተዋል ነው ያሉት።

በመደመር እሳቤ የተጀመሩት እነዚሁ ፕሮጀክቶች ለነገው ትውልድ የሚተላለፉ ቅርሶች መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ዝርያው እየተመናመነ የመጣው የአፍሪካ የዝሆን ዝርያን ጨምሮ እንደ ጎሽ፣ ዲፋርሳ፣ ከርከሮ፣ ሳላና አጋዘን ያሉ የዱር እንስሳት የሚገኙበት ሲሆን በደን ሽፋኑ ይበልጥ ጎልቶ ስሙ የሚነሳ እንዲሁም በውስጡ የሚያቋርጡ በርካታ ወንዞችና አምስት ሃይቆችም ይገኛሉ።

እንደኢዜአ ዘገባ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካል በሆነው የኮይሻ ፕሮጀክት ፓርኩን መጎብኘት የሚያስችል መሠረተ-ልማት በማሟላት የአካባቢውን የቱሪዝም ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎች ተከናውነዋል።