የጨው ቅነሳ የሚዲያ ዘመቻ መርሀ ግብር ይፋ ሆነ

የካቲት 09/ 2013 (ዋልታ)- “ጨው ሞቅ ያለበት ምግብ አይመገቡ” በሚል መሪ ቃል በአለም ለ3ኛ ጊዜ በአፍሪካ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚዲያ ዘመቻ ይፋ ሆነ፡፡

የጨው መጠንን በየዕለቱ ከምንመገብባቸው ምግቦች ውስጥ ጨው መቀነስን አስመልክቶ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያለመ የሚዲያ ንቅናቄ መሆኑን የጤና ሚንስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ አስታውቀዋል፡፡

ንቅናቄውም በጤና ሚንስቴር ፣በአለም የጤና ድርጅት እና የቫይታል ስትራቴጂ ኢንሼቲቭ የሆነው ሪሶልቭ ቱ ሴቭ ላይቭስ በመቀናጀት ያዘጋጁት መሆኑን የኢንሸቲቩ ካንትሪ ዳይሬክተር ዶ/ር ዳዊት ታጠቅ ገልፀዋል፡፡

አያይዘውም ምግብን በቤት ውስጥ በምናዘጋጅበት ወቅት የምንጨምረውን የጨው መጠን በግማሽ እንዲቀንሱ ለማስገንዘብ ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከፍተኛ የጨው መጠንን መውሰድ ለደም ግፊት ቀጥተኛ መንስኤ መሆኑን አንስተው የደም ግፊት በሽታ በሃገራችን በየዓመቱ በልብ ህመም እና በስትሮክ ለሚከሰተው ሞት ዋነኛ መንስኤ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በተመሳሳይ የዓለም የጤና ድርጅት ተወካይ ዶ/ር ኢስተርን አቼንግ የዓለም የጤና ድርጅትና የጤና ሚንስቴርን ጥናት ጠቅሰው፤ በኢትዮጲያ አንድ ሰው በየቀኑ በአማካይ 8 ነጥብ 3 ግራም ጨው እንደሚጠቀምና ይህ ቁጥር በቀን የሰው ልጅ መመገብ ከሚገባው 5 ግራም ከፍ ያለ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በመጨረሻም የደም ግፊት እና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ህብረተሰቡ በሚመገበው ምግብ ውስጥ ምን እንዳለ ማወቅ፣ ከሱፐር ማርኬቶች ወይም ከገበያዎች የሚገዟቸውን የታሸጉ ምግቦች፣ እንዲሁም በቤት ውስጥ አዘጋጅተው ከሚመገቧቸው ምግቦች ውስጥ ምን አይነት ንጥረ ነገሮች እንዳሉባቸው ጠንቅቆ ማወቅ ይጠበቅበታል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ደረጀ ይህ አይነቱን የጨው አጠቃቀም በግማሽ መቀነስና አመጋገባችንን ወደ ጤናማ የአመጋገብ ዘዴ መቀየር የደም ግፊት፣ ስኳር እና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለማስወገድ የተሻለ አማራጭ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡
(በአመለወርቅ መኳንንት)