ታኅሣሥ 11/2015 (ዋልታ) የጮቄ ተራራ ቱሪዝም መንደር በተባበሩት መንግስታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት (UNWTO) የ2022 ምርጥ የቱሪዝም መንደር ተብሎ እውቅና ተሰጠው።
ከአዲስ አበባ በስተሰሜን ምዕራብ በ300 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኘው የጮቄ መንደር በምዕራብ ጎጃም ዞን ደጋ ዳሞት ወረዳ ይገኛል፡፡
የሙሉ ኢኮሎጅን እሳቤ መሰረት በማድረግ ማኅበረሰብን መሰረት ያደረገ ቱሪዝም፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ኢኮ ቱሪዝም እና ዘላቂ አካባቢ ጥበቃን መሰረት ያደረገ አኗኗርን የሚተገብር ማኅበረሰብ የፈጠረ መንደር መሆኑም ታውቋል።
በኢትዮጵያ ሦስተኛው ከፍተኛ ተራራ የሆነው ጮቄ ተራራ ላይ የሚገኘው የቱሪዝም መንደር በዋናነት ለገጠር ልማት አንቀሳቃሽ ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል፡፡
የቱሪዝም መንደሩ የሀገር ባህልና የተፈጥሮ ሀብቶቿን፣ ትውፊቶቹን እና ማህበረሰቡን መሰረት ያደረጉ እሴቶቿን፣ የቱሪዝም ምርቶች እና የአኗኗር ዘይቤዎችን ያስታዋውቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተመላክቷል፡፡
ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ የወንጪ ሃይቅ በምርጥ የዓለም ቱሪዝም መንደርነት እውቅና ማግኘቱ ይታወሳል።