ጥቅምት 9/2014 (ዋልታ) የፀጥታ አካላትን ማጠናከርና አቅማቸውን ማጎልበት ለሀገር ሰላምና ደህንነት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለፁ፡፡
አፈ ጉባኤው ይህንን ያሳወቁት በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መስሪያ ቤት ተገኝተው በዛሬው ዕለት የተሰሩ የሪፎርም ስራዎችን በጎበኙበት ወቅት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስና የክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች በአደረጃጀት፣በትጥቅና በአሰራር የበለጠ ስታንዳርዱን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ምክር ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግም አሳውቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በተሰሩ አጠቃላይ ስራዎችን በሚመለከት ማብራሪያ የቀረበ ሲሆን፣ አፈ ጉባኤው ተቋሙ ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል ብሎም የስራ አካባቢን ውብና ምቹ ለማድረግ ላከናወነው ተግባር አድናቆት እንዳላቸው ገልፀው፣ ለተሰራው ስራ በራሳቸውና በምክር ቤቱ ስም አመስግነዋል፡፡
ከሶስት ዓመት ወዲህ በርካታ ለውጦችን በየተቋማቱ ለማምጣት አመራሩ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል ያሉት አቶ ታገሰ፣ በአስተዳደርና ፀጥታ ዘርፍም ተጨባጭ የሆኑ ለውጦችን ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡
ሰላም ሲኖርና የህዝቡ ደህንነት ማስጠበቅ ሲቻል ነው ሌሎቹን ስራዎች ማስኬድ የሚቻለው ያሉት አፈ ጉባኤው፣ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ላይ የሚሰራ የሪፎርም ስራ ለሀገር ደህንነት፣ለሉዓላዊነትና ብልፅግና ትልቅ መሰረት ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ፣ የህዳሴ ግድብ ግምባታ በተሟላ መልኩ እንዲከናወን እንዲሁም ሌሎች ሀገራዊ አጀንዳዎች በስኬት እንዲጠናቀቁ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡
ሀገራዊ ምርጫ እንዳይካሄድና መንግስት እንዳይመሰረት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ያሉ አንዳንድ አካላት የፈጠሩትን ተግዳሮቶችን በመከላከል የፀጥታ አካሉና ህዝቡ ያሳዩትን ትጋትና ፅናት መቸም የማይረሳና ታሪካዊ ነው ብለዋል፡፡
የወንጀል ምርመራና የመከላከል ብቃቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሳደግ በሚቀጥሉት አምስት ዓመት ውስጥ ተጨማሪ የተሳኩ ተግባራትን እንደሚያከናውን ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡
የፖሊስ ሰራዊቱ የበለጠ በስነ-ምግባር የበቃ እንዲሆን እና አገልግሎቶቹ በቴክኖሎጂ የተደገፉ እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ ተቋሙ የጀመራቸው ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ማለታቸውን ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።