የፈጠራ ሃሳብ ላላቸው ቡድኖች የ5 ሺሕ ዶላር ድጋፍ የሚያስገኝ ስልጠና እየተሰጠ ነው

ሐምሌ 26/2014 (ዋልታ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከተስፋ ኢኤልጂ ስራ ፈጣሪዎች ፕሮግራም ጋር በመተባበር የፈጠራ ሀሳብ ያላቸውን አካላት አቅም የሚያጎለብት የአምስት ቀን ስልጠና እየሰጠ ነው።

በሚኒስቴሩ የምርት እና አገልግሎት ምህንድስና ዳይሬክተር ብርሃኑ አበበ እንደተናገሩት ስልጠናው ከአገሪቱ የእድገት አጀንዳ ጋር የተጣጣሙ ብሔራዊ የፈጠራ እና የቴክኖሎጂ ምርምር እና ልማት ፕሮግራሞችን ለማዘጋጀት እና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እየተሰራ ያለው አካል ነው።

ዳይሬክተሩ አክለውም ስልጠናው በሀገሪቱ ውስጥ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት ስራዎችን ከማስተዋወቅ አንጻር ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቁመው የሀገሪቷን ማህበራዊ እና ልማት ስራዎች ዕውን ለማድረግ ፈጠራና ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረጉ ተግባራትን ማስተባበር፣ ማበረታታት እና የመደገፍ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡

የስዊዘርላንድ ተስፋ ኢኤልጂ ስራ ፈጣሪዎች ፕሮግራም ተወካይ ኦሊቨር ፍሉይኪገር በበኩላቸው የትብብር ፕሮግራሙ የኢትዮጵያን ህዝብ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ጤናና የመሳሰሉት ዘርፎች ለማሻሻል እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ፈጠራን በማጎልበት እና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ የፈጠራ ስራዎች አስቻይ ከባቢ ሁኔታን በመገንባት ረገድ ትልቅ ሚና እንዲጫዎት በማሰብ ስልጠናው እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል፡፡

ከመላው ኢትዮጵያ ከተውጣጡ 90 ተወዳዳሪዎች መካከል ባቀረቡት የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሀሳብና ፕሮጀክቶች ተወዳድረው የተመረጡ አስር ቡድኖች በስልጠናው እየተሳተፉ እንደሚገኙ የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።

ሰልጣኞች ከስልጠናው በኋላ በተፈጠረላቸው አቅም ፕሮጀክቶቻቸውን የሚያዳብሩ ሲሆን የላቀ ውጤት ለሚያመጡ 5 ፕሮጀክቶች ለእያንዳዳቸው የ5 ሺሕ ዶላር ድጋፍ እና ሌሎች የድጋፍ ስራዎች ይደረግላቸዋል።

የፈጠራ ውድድሩ በጤና እና ግብርና ዘርፎች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን የሚፈቱ የድሮን፣ ሶፍትዌር እና አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ፕሮጀክቶች ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡