ታኅሣሥ 22/2014 (ዋልታ) የፌዴራል መንግስት ከጥቅምት እስከ ኅዳር 2014 ባለው ሁለት ወራት ብቻ ከሀገር ውስጥ ገቢ ማለትም ታክስና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች 70 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ እንደቻለና ይህም የእቅዱ 89 ነጥብ 3 በመቶ እንደሆነ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በ2014 በጀት ዓመት 2ኛ ሩብ ዓመት የ100 ቀን እቅድ አፈጻጸም በገንዘብ ሚኒስቴር በተገመገመበት ወቅት እንደተገለጸው በፌዴራል መንግስት ከሀገር ውስጥና ከልማት አጋሮች ለመሰብሰብ የታቀደውን የመንግስት ገቢ ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት መደረጉ እና አፈጻጸሙም መልካም እንደነበር ሚኒስቴሩ አመልክቷል።
ከጥቅምት እስከ ታህሳስ 2014 ዓ.ም ባለው ወቅት ከበይነ-መንግሥታዊ ተቋማት እና ከመንግሥታት ትብብር የልማት አጋሮች በእርዳታና በብድር በድምሩ 364 ሚሊዮን ዶላር የተገኘ ሲሆን 255.6 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ወደ ሀገር ውስጥ ፈሷል።
በተመሳሳይ መልኩ ባለፉት ሶስት ወራት ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ትርፍ ድርሻ 3.8 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ተችሏል ነው የተባለው።
የመንግስት ወጪን በተመለከተም በዚሁ ወቅት ለፌዴራል መንግስት 73.3 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን ለብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት 33.6 ቢሊዮን ብር ወጪ በመደረግ በድምሩ 106.9 ቢሊዮን ብር ለፌዴራልና ለክልል መንግስታት ክፍያ መተላለፉ ተመላክቷል።
ትኩረት ለሚሰጣቸው የመንግስት ወጪ ፍላጎቶች ቅድሚያ በመስጠት የተገኘውን ጥሬ ገንዘብ በአግባቡ ማስተዳደር እንደተቻለ ተጠቁሟል።
በመቶ ቀኑ እቅድ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት፣ ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር እንዲሁም ከገንዘብ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት የተውጣጡ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን በእቅድ አፈጻጸሙ ላይ የታዩ ጠንካራ ጎኖች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ደካማ ጎኖች ደግሞ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድባቸው አስተያየትና አመራር ተሰጥቷል።