ሚያዝያ 13/2013 (ዋልታ) – የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች በጀታቸውን ለታለመለት አላማ በጥንቃቄና በቁጠባ አገልግሎት ላይ ማዋል እንደሚጠበቅባቸው የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ አሳሰቡ።
የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የ2014/2015 በጀት አመት የፕሮግራም በጀት ስሚ መድረክ በበይነ መረብ መካሄድ ጀምሯል።
ከሚያዚያ 13 እስከ ሚያዚያ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ለሰባት ቀናት በሚካሄደው የበጀት ስሚ መድረክ 73 የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የ2014/2015 በጀት አመት የፕሮግራም በጀታቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን፣ ባለበጀት መስሪያ ቤቶቹ በጀታቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ባስቀመጠው የበጀት ጣራ መሰረት ሰርተው እንዲያቀርቡ ይጠበቃል።
የበጀት ስሚ መድረኩን የሚመሩት የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ውይይቱን ሲከፍቱ ከፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚጠበቅ አንስተዋል።
የበጀት ስሚ ዋናው ዓላማ የሚቀርቡ የበጀት ጥያቄዎች የመንግሥት ፖሊሲ የተከተሉ መሆኑን፣ ፈጣን፣ ፍትሃዊና ዘላቂ ዕድገት ለማምጣት በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ መሰረት መቅረባቸውን ለመገምገም መሆኑን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።