የፌዴራል ዋና ኦዲተር ከተፈቀደላቸው በጀት በላይ የተጠቀሙ 24 ተቋማት መገኘታቸውን አስታወቀ

ሰኔ 14/2014 (ዋልታ) የፌዴራል ዋና ኦዲተር ከተፈቀደላቸው በጀት በላይ የተጠቀሙ 24 ተቋማት መገኘታቸውን አስታውቋል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስርያ ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ እያቀረበ ባለው ሪፖርት በ24 መሥሪያ ቤቶች በልዩ ልዩ የሒሳብ መደቦች ሳያስፈቅዱ እና በጀት ሳያዘዋውሩ ከተደለደለው በጀት በላይ ወጪ የሆነ ሒሳብ መገኘቱን አረጋግጧል፡፡

ከመደበኛ በጀት 645 ሚሊየን 198 ሺሕ 927 ብር በላይ ሆኖ መገኘቱን ነው ያረጋገጠው።

በልዩ ልዩ የሒሳብ መደቦች ከተፈቀደላቸው በጀት በላይ ከተጠቀሙ መሥሪያ ቤቶች መካከል የኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርስቲ፣ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፣ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፣ ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፣ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ፣ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ እና ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ተካተዋል።

ተቋማቱ በየሒሳብ ኮዶቹ ከተፈቀደው በጀት ከ10 በመቶ በላይ ያልተጠቀሙበትን ብቻ በመውሰድ፤ በድምሩ ብር 21 ቢሊየን 12 ሚሊየን 778 ሺሕ 873 በላይ ብር ያልተሠራበት በጀት ተገኝቷል ማለቱን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።