የፌዴራል ፖሊስ አባላት የመዲናዋን ሠላምና ፀጥታ ለመጠበቅ ሌት ተቀን እየሰሩ መሆናቸው ተገለጸ

ኅዳር 6/2014 (ዋልታ) የፌዴራል ፖሊስ አመራርና አባላት በተለያዩ ግንባሮች ከሚያደርጉት ተጋድሎ ጎን ለጎን ከተማዋን ከወራሪው የጁንታ ተላላኪዎች እና ከሰርጎ ገቦች ለመጠበቅ እየሰሩ እንደሚገኙ ተገለጸ።

በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተመድበው የሚሰሩ የፌዴራል ፖሊስ አባላት አሸባሪውን የሕወሓት ቡድንና ተላላኪውን ሸኔን ለመደምሰስ ከሚያካሂዱት የኅልውና ዘመቻ በተጨማሪ የአዲስ አበባን ሠላምና ፀጥታ ከጥፋት ኃይሎች ለመጠበቅ ሌት ተቀን እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ከወረራቸው አካባቢዎች ለቆ እስካልወጣ ድረስ የህልውናው ዘመቻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት አመራርና አባላት ለዘመቻው መሳካትም እስከህይወት መስዋእትነት ለመክፈል ቁርጠኛ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ህብረተሰቡም ለፀጥታ ኃይሉ የሚያደርገው እገዛ ለከተማዋ ፀጥታ ጉልህ ሚና እንዳለው የገለፁት የፖሊስ አባላት በቀጣይም የህብረተሰቡ እገዛ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በአሸባሪው የጁንታ ቡድን የተከፈተውን ወረራ በመቀልበስ አገሪቱ የጀመረችውን የብልፅግና ጉዞ በተሳካ ሁኔታ ለማስቀጠል በቁርጠኝነት እየሰራን ነው ማለታቸውን ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።