የፌዴራል ፖሊስ ኮኬይን የተሰኘ አደንዛዥ ዕፅ በቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ በቁጥጥር ስር አዋለ

መጋቢት 13/2014 (ዋልታ) የኢትዮጰያ ፌዴራል ፖሊስ መጋቢት 12 ቀን 2014 ዓ.ም ኮኬይን የተሰኘ አደንዛዥ ዕፅ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ውስጥ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገለጸ፡፡

ሦስት የናይጄሪያ ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች መነሻቸውን ብራዝል-ሳኦፖሎ በማድረግ በኢትዮጵያ በኩል ወደተለያዩ አገራት 1 ሺሕ 895 ጥቅል ፍሬ (42 ኪሎ ግራም) የሚመዝን ኮኬይን በቦርሳ ይዘው ለማለፍ ሲሞክሩ በቁጥጥር ስር መዋላችውን የቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ አደገኛ ዕፅ ቁጥጥር ማስተባበሪያ ኃላፊ ኢንስፔክተር አዲሱ ባለኒ ገልፀዋል፡፡

ግለሰቦቹ በአየር መንገዱ ጣቢያ ውስጥ ግርግር በመፍጠር እና ከሰራተኞች ጋር በመጋጨት ለማምለጥ ሙከራ ቢያደርጉም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ መነሻዋን ብራዝል ሳኦፖሎ መዳረሻዋን ደግሞ በኢትዮጵያ በኩል ዱባይ ለማድረግ 1 ሺሕ 49 ጥቅል ፍሬ (21 ኪሎ ግራም ከ380 ግራም) የሚመዝን ኮኬይን የያዘች ብራዚላዊት የኢትዮጰያ ፌዴራል ፖሊስ አባላት ባደረጉት ፍተሻ የካቲት 24 ቀን 2014 ዓ.ም በቁጥጥር ስር መዋል መቻሏን ኃላፊው አስታውሰዋል፡፡

በአጠቃላይ በ15 ቀናት ውስጥ 2 ሺሕ 44 ጥቅል ፍሬ (63 ኪሎ ግራም ከ380 ግራም) ኮኬይን ተይዟል ማለታቸውን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡

የአደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ተይዘው እና ወደ ፍርድ ቤት ቀርበው ውሳኔ ሳያገኙ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆላቸው ከእስር ከወጡ በኋላ በቀጠሮ ቀን ተመልሰው ሳይቀርቡ መቅረታቸው እና አደንዛዥ ዕፁን ይዘው ለሚገኙ ሰዎች የሚሰጥ ውሳኔ አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት ዝውውሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልፀዋል፡፡