የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የሞባይል መመርመሪያ መሳሪያ ግዢ ፈጸመ

የፌዴራል ፖሊስ የሞባይል መመርመሪያ

ሐምሌ 08/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የዲጂታል ፎረንሲክ ምርመራ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ የሞባይል መመርመሪያ መሳሪያ (celebrate Machine) ግዢ ፈጸመ፡፡

ከእስራኤል ለተገዛው መሳሪያ 110 ሺህ 600 ዶላር ወጪ የተደረገበት ሲሆን፣ ወደ ስራ ለማስገባት ለሙያተኞች ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም መንግስቴ የስራ ዘርፉን ይበልጥ ለማደራጀት በርካታ ገንዘብ ወጪ ተደርጎበት የተገዛ በመሆኑ ባለሙያዎቹ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲያውሉ አሳስበዋል፡፡

የበይነ መረብ ወንጀሎች ምርመራ ዲቪዥን ሀላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ዳኜ ነጋሽ በበኩላቸው፥ መሳሪያው ዘመናዊነትን የተላበሰና አሁን ዓለም በዘመናዊ መንገድ የሚጠቀመው በመሆኑ ማናኛውንም ሞባይል መመርመር የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይም የወንጀል ምርመራ ቢሮው የዲጂታል ፎረንሲክ ምርመራን በቴክኖሎጂ ለማስደገፍ የተለያዩ ዘመናዊ የሆኑ የመመርመሪያ መሳሪያዎችን ወደ ስራ ለማስገባት እየሰራ እንደሆነ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡