የካቲት 04/2013 (ዋልታ) – የፌዴሬሽን ምክር ቤት የ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ዋና ዋና የስራ ዕቅድ አፈጻጸሙን ገምግሟል።
ምክር ቤቱ የሕግ የበላይነት እንዲከበር ሕገ መንግስታዊ ውሳኔዎችን ማሳለፉ እንዲሁም 15ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል እኩልነትንና ሕብረብሄራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ በልዩ ሁኔታ መከበሩ በጥንካሬ ተነስቷል።
በተጨማሪም የፌደራል እና ክልል መንግሥታት ግንኙነት ስርዓት አዋጅ መውጣቱ እና መተግበር መጀመሩ በምክር ቤቱ አሰራር ላይ ትልቅ ለውጥ ማምጣት መጀመሩ እንዲሁም የምክር ቤቱን ፓርላሜንታዊ ዲፕሎማሲ ለማጠናከር ከተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ጋር ውይይት መደረጉ ተወስቷል።
ሕገ መንግስቱ ለሴቶች ያጎናፀፋቸው የእኩልነት መብቶች እንዲረጋገጡ እና ከፌደራል ስርዓቱም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከሚመለከታቸው አካላትጋር የምክክር መድረክ መካሄዱም ተጠቅሷል።
ለ22 ዓመታት ሳይሻሻል የቆየውና ግልጸኝነት የጎደለው የጋራ ገቢዎች ማከፋፈያ ቀመር ተሻሽሎ ግልጸኝነት ባለው አዲስ ቀመር መተካቱም እንደ ስኬት ተነስቷል፡፡
ይህም የሀብት ክፍፍል ፍትሓዊነት እና የፌደራል ሥርዓቱ ቀጣይነት እንዲረጋገጥ ጉልህ ሚና ይጫወታል ተብሏል፡፡
አዲሱ የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ቀመር የክልሎች የገቢ አሰባሰብ አቅም በብዙ እጥፍ እንዲያድግ ያደርጋል ነው የተባለው።
በተጨማሪም በክልሎች መካከል ጤናማ ግንኙነት፣ ጠንካራ ሕብረብሔራዊ አንድነትና መተማመን እንዲጎለብት ያስችላል መባሉን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።