የፌዴሬሽን ምክር ቤት 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ነው

ሐምሌ 7/2014 (ዋልታ) የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስድስተኛ የፓርላማ ዘመን 1ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን ማካሄድ ጀመሯል፡፡

ምክር ቤቱ ስድስተኛ የፓርላማ ዘመን 1ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ በግፍ ለተጨፈጨፉ ንጹሃን ዜጎች የህሊና ጸሎት በማድረግ ጉባኤውን የጀመረ ሲሆን 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ ቃለ ጉባኤን መርምሮ በማጽደቅ ውይይቱን ቀጥሏል።

በመቀጠልም የአራቱን ቋሚ ኮሚቴዎችን እና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤን የ2014 ዓ.ም የአፈጻጸም ሪፖርቶች፣ ከሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል በተባሉ የውሳኔ ሐሳቦች፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም በሚል ውሳኔ በተሰጣቸው እና ለምክር ቤቱ በይግባኝ በቀረቡ አቤቱታዎች ላይ በመወያየት ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተጨማሪም የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር 1261/2013 ለማስፈጸም የተዘጋጀ ረቂቅ ደንብ፣ ውስን ዓላማ ያላቸው የድጎማ በጀትና የፌዴራል መሠረተ ልማት ስርጭት ፍትሐዊነት የክትትል ሥርዓትን ለማስፈጸም የተዘጋጀ ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ እንደሚያጸድቅ የሚጠበቅ ሲሆን የተለያዩ ሹመቶችንም ያጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW