ሰኔ 20/2013 (ዋልታ) – የባለጉዳዮችን የፍርድ ቤት ቀጠሮ አጭርና ቀልጣፋ የሚያደርግ አዲስ የአሰራር መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በቅርቡ የፀደቀውን የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ በሚቻልበት ዙሪያም ዳኞች፣ ጠበቆችና የአስተዳደር አካላት ምክክር አድርገዋል።
መመሪያው የፍርድ ቤቶችን ቀጠሮ መዘግየት በማስቀረት ረገድ ከፍተኛ ሚና አለው ተብሏል፡፡
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ፉአድ ኪያር በፍርድ ቤቶች ያለው የመዝገብ ክምችት ከመጠን ያለፈ መሆኑ የፍትህ ስርአቱን ታአማኝነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባው መሆኑን ጠቅሰው፤ አዲስ የፀደቀው መመሪያ የጉዳዮችን መጓተትንና መዘግየትን እንደሚያሻሽለው ተናግረዋል፡፡
የመመሪያው አሰራርም በጉዳዮች ላይ የጊዜ ገደብ በማስቀመጥና እንደየመደባቸው በማከናወን ያልተጓተተ ፍትህ ለዜጎች ተደራሽ ማድረግን ኢላማ ያደረገ ነው ተብሏል።
በመሆኑም ዜጎች በፍትህ ስርአቱ ላይ ያላቸውን አመኔታና እርካታ ለመጨመር በተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀውን የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ ፍርድ ቤቶች ተግባራዊ ሊያደርጉ እንደሚገባ ነው የተገለጸው፡፡
የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት እያሻሻላቸው የመጡ አዋጆች የዳኝነት ስርአቱን ነፃና ገለልተኛ በማድረግ የተሻለ ፍትህ እንዲሰጥ እያስቻሉ ተብሏል፡፡
(ደምሰው በነበሩ)