የፍቅር ጥያቄውን ባለመቀበሏ የሥራ ባልደረባውን የገደለ ግለሰብ በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነበት

ነሐሴ 11/2014 (ዋልታ) ባለትዳር ለሆነች የሥራ ባልደረባው ያቀረበውን የፍቅር ጥያቄ ባለመቀበሏ ግድያ የፈጸመው ግለሰብ በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነበት፡፡

የዐቃቤ ህግ መዝገብ ላይ እንደተገለጸው ጌታቸው አለምፀሃይ ክፍሉ የተባለው ተከሳሽ ጥር 2/2011 ዓ.ም ከረፋዱ 5፡30 በንፋስ ስልክ ላፍቶ ወረዳ 01 ልዩ ቦታው ሳባ ህንፃ ውስጥ በሚገኘው የንፋስ ስልክ ላፍቶ ወረዳ 01 ፋይናንስ ቢሮ ውስጥ የሥራ ባልደረባው የነበረችውን ሟች መዓዛ ካሳ የፍቅር ጥያቄ አቅርቦላት ባለትዳር እንደሆነች ብትገልፅለትም የግድ አብረው መሆን እንዳለባቸው ቢወተውታትም ፈቃደኛ ባለመሆኗ ምክንያት በሥራ ገበታዋ ላይ እያለች በቢላ እያባረረና ለማምለጥ ከቢሮ ስትሮጥ በወደቀችበት በቀኝና በግራ ሆዷ ላይ ደጋግሞ በመውጋት የሆድ ዕቃዋ ወደ ውጪ ወጥቶ ህይወቷ እንዲያልፍ በማድረጉ በፍትህ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ ክስ ተመስርቶበታል።

ጌታቸው አለምፀሃይ ክፍሉ

በአዲስ አበባ ፖሊስ ምርመራ ተጣርቶበት በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በከባድ የሰው መግደል ወንጀል በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በዐቃቤ ህግ ክስ ቀርቦበታል ነገር ግን ተከሳሽ በምርመራ ላይ እያለ ከእስር በማምለጡ ምክንያት ክሱ በሌለበት እንዲታይ ተደርጓል፡፡

ተከሳሹ ሆነ ብሎ የተሰወረ በመሆኑ ዐቃቤ ህግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ በሚያሰማበት ጊዜ የዐቃቤ ህግን ማስረጃ የመጠየቅ እና የመመርመር መብቱ ታልፎ ፍ/ቤቱ በዐቃቤ ህግ የቀረበው ማስረጃ በበቂ ሁኔታ ተከሳሹ ድርጊቱን የፈጸመ መሆኑን ያስረዳ በመሆኑ እንዲሁም መብቱን ጠብቆ የዐቃቤ ህግን ክስ እና ማስረጃ ያላስተባበለ በመሆኑ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት ነሐሴ 4/2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኖበታል።

ጌታቸው አለምፀሃይ ክፍሉ ከላይ በምስሉ ላይ ያለው ሰው ሲሆን በምርመራ ወቅት ከእስር አምልጦ ተደብቆ እንደሚገኝና ያለበትን አድራሻ የሚያውቅ ካለ ጥቆማውን ለአዲስ አበባ ፖሊስ ወይም ለፍትህ ሚኒስቴር እንዲያሳውቅ መጠየቁን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW