የፍትህ ሚኒስቴር የዜጎችን መብት ለማስከበር አስቸጋሪ የነበሩ ህጎችን በማሻሻል ለውጥ ማምጣት እንደተቻለ ገለጸ

መጋቢት 19/2014 (ዋልታ) የዜጎችን ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተገቢው ለማስከበር አስቸጋሪ የነበሩ ህጎችን በማሻሻል ለውጥ ማምጣት መቻሉን የፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩና በክልል ፍትህ ቢሮዎች በህግና ፍትህ ማሻሻያ ዙሪያ የሚመክር መድረክ ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ተጀምሯል።
በመድረኩ ላይ የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ዓለምአንተ አግደው እንዳሉት ባለፉት ሦስት የለውጥ ዓመታት የህግና ፍትህ ማሻሻያዎች እንዲሁም የዘርፉ ተቋማት ግንባታ ሥራዎች ተከናውነዋል።
በዚህም የዜጎችን ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተገቢው ለማስከበር አስቸጋሪ የነበሩ ህጎችን በማሻሻል ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሉን አስታውቀዋል።
ከተሻሻሉት ህጎች መካከል የሲቪክ ማኅበራት፣ የአስተዳደርና የጠበቆች አዋጅ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ሌሎችም እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
የፍትህ ተቋማት ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሙያዊ ነጻነታቸውን ጠብቀው እንዲሰሩም አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
የዛሬው መድረክ ዓላማም በፌዴራል ደረጃ ሲከናወን የነበረው የህግና የፍትህ ማሻሻል ሥራዎች ክልሎች ከራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ተግባራዊ እንዲያደርጉ ለማስቻል የተመቻቸ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል።
በተለይ ማሻሻያ ተደርጎባቸው በፌዴራል ደረጃ ተፈጻሚ እየሆኑ ያሉ የህግና የፍትህ ሥራዎች በክልሎችም ተግባራዊ የሚሆኑበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር መሆኑን ገልጸዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲያዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እፀገነት መንግስቱ በበኩላቸው ”ምክር ቤቱ ህጎች በተገቢው ሁኔታ ተግባራዊ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ከትትልና ቁጥጥር ያደርጋል” ብለዋል፡፡
ምክር ቤቱ የተለያዩ ህጎችን ከማውጣት በተጨማሪ በአግባቡ ተግባራዊ መሆናቸውን በክትትልና ቁጥጥር ሥራው ያረጋግጣል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ለሦስት ቀናት በሚቆየው የምክክር መድረክ ላይ የፌዴራል ከፍተኛ አመራሮችና የክልሎች የፍትህ ቢሮ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛል።