የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ ሁሉንም አይነት አሻራ በማሳረፍ የኢትዮጵያን ሕልውና እንደሚያስጠብቅ ገለፀ

ነሀሴ 07/2013 (ዋልታ) – እንደ አረንጓዴ አሻራ ሁሉ ሁሉንም አይነት አሻራ በማሳረፍ የሀገራችንን ሕልውና እናስጠብቃለን ሲል የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ገለጸ።

በኢትዮጵያ ላይ የዘመቱ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ተዕጽኖ ላይ የዲፕሎማሲ አሻራ እንደሚያሳርፍም አረጋግጧል።

የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ ዛሬ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን በማስመልከት መግለጫ ሰጥቷል።

የቡድኑ ሰብሳቢ ደራሲ ጌታቸው በለጠ በ2004 የተቋቋመው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ከተቋቋመለት ዓላማ አንፃር በውጭ ጉዳይ በተለይም በጎረቤት አገራት ጉዳዮች ያተኮረ እንደነበረ ገልጸዋል።

ትኩረቱን ከሀገር ውጭ ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ዓላማውን ከወራት በፊት የከለሰው ቡድኑ በመጀመሪያው የትግራይ ህዝብን ለማወያየት ሲንቀሳቀስ በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈፀመው ጥቃት ሁኔታውን እንደተቀየረው አስታውሰዋል።

ቡድኑ በርካታ የወደፊት ዕቅዶች እንዳሉት እና ለአብነትም በሀገራዊ ስነ-ምግባር፣ በፖለቲካ፣ በባህልና እሴቶች ላይ እንደሚሰራ ገልፀዋል።

በወቅታዊ ጉዳይ ከመንግሥት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጋር እንዳይጋጭ በሚል ቢዘገይም የቡድኑ አባላት በተናጠልና በቡድን በተለያዩ ሚዲያዎች ውይይቶችን ማካሄዳቸውን አስታውሰዋል።

እንደ አረንጓዴ አሻራ ሁሉ በኢትዮጵያ ታሪክ የደም አሻራ አሳርፈን የአገር ሕልውናን እናስጠብቃለን ያሉት አቶ ጌታቸው አገር ለማዳን የደም አሻራ፤ በዓለም አቀፉ ሚዲያም የተፅዕኖ አሻራ እናሳርፋለን ብለዋል።

ግልጽ አቋም የያዙና ከሙያው ስነ ምግባር ያፈነገጡ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ላይ የዘመቱ በመሆኑ አካሄዳቸውን ‘ውሸት ነው’ ብለን አሻራ እናኖራለን ሲሉም አክለዋል።

የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ ሰብሳቢ “ከዚህ በኋላ አገር የመታደግ፣ ሕልውና የማስከበርና ታሪክ የማስቀጠል ድርሻ ወድቆብናል” ነው ያሉት።

አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን እንዲሁም የትግራይን ሕዝብ እያመሰ በመሆኑ እስከመጨረሻው እንዲጠፋ ፊት ለፊት መጋፈጥ ተገቢ እንደሆነም አመልክተዋል።

ባህላዊውን እርቅ ገፍቶና የእናቶችን ልመና ገፍትሮ ወደ ጦርነት የገባን አሸባሪ ቡድን በሌላ ባህላዊ እርቅ ለመፍታት ሁለተኛ እድል አንሞክርም ብለዋል።

በኢትዮጵያ ላይ የተጋረጠውን ወቅታዊ የህልውና ስጋት ለመመከት ሁሉም የጋራ አቋም በመያዝ ወደ አንድነት የመጣ በመሆኑ “መርገምትም በረከትም አለው” ብለዋል።

የቡድኑ አባል አርቲስት ደበሽ ተመስገን በበኩሉ ፖለቲካና ጣልቃ ገብነት የሌለበት የፐብሊክ ዲፕሎማሲው ግብፅን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ተዘዋውሮ በዲፕሎማሲው መስክ ውጤታማ ስራዎችን ሰርቷል ብሏል።

“ጥበብን ለሠላም” በሚል እንቅስቃሴ መጀመሩንና በአልጀዚራ የሚቀርብ ዘጋቢ ፊልም በመሰራት ላይ መሆኑንም ጠቁሟል።

በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ የሕዝብ ወገንተኛ በመሆን ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎችን ለመመከት ከሕዝብ ጋር እንቆማለን ብሏል።

የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ አባላት ወይዘሮ እንግዳዬ እሸቴ እና አቶ ጥበቡ በለጠ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትና ኢትዮጵያዊያንን እርስ በእርስ የማጋጨት ሴራ መመከት እንደሚገባ አመለክተዋል።

በኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመመከት በጋራ መቆም፤ የሕልውና ጉዳይ በመሆኑም ሁሉም አገሩን ለማዳን ዘብ ሊቆም ይገባልም ብለዋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ