የፈረንሳይዋ ፓሪስ ከመቶ ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በየአራት ዓመቱ የሚደረገውን ኦሊምፒክ ታስተናግዳለች፡፡ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ሊደረግም ጥቂት ሰዓታት ብቻ ቀርተውታል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ክንውን በሚደረግበት በዚህ ቀን አዳሩን ጀምሮ የፈረንሳይ የፈጣን የባቡር ሀዲዶች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል፡፡ በዚህም ፈረንሳይ በመላው ሀገሪቷ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቶቿን ለማቋረጥ ተገዳለች፡፡
ይህ ጥቃት ሆን ተብሎ በተቀናጀ መልኩ ፈረንሳይ ለ10 ዓመታት በጥንቃቄ ስትዘጋጅበት የቆየችውን የኦሊምፒክ ውድድር ለማስተጓጓል እንደተፈጸመም የፈረንሳይ ስፖርት ሚኒስትር ተናግረዋል፡፡
የአገሪቷ የባቡር ትራንስፖርት ድርጅት ፓሪስን ከዋና ዋና ከተሞች ጋር የሚያገናኙት መስመሮች ላይ ከበድ ያለ ጥቃት እንደተሰነዘረበት ገልጿል፡፡ በርካታ የኦሊምፒክ ውደድሩን ለመካፈል የሚመጡ መንገደኞችም ጉዟቸው ሊራዘም ግድ ሆኗል፡፡
እግር ኳስን ጨምሮ በርከት ያሉ የኦሊምፒክ ውድድሮችም ከፓሪስ ከተማ ውጪ እንደሚካሄዱ ይጠበቃል፡፡ ወድድሮቹ ሊካሄድባቸው የሚችሉባቸው ከተሞችን የሚያገናኙ የባቡር መስመሮች ላይ ጥቃቶቹ ተሰንዝረዋል፡፡
ሀዲዶቹን አንድ በአንድ ለመስራት እየጣረ እንደሆነ የገለጸው የባቡር ትራንስፖርት ድርጅቱ በአደጋው አስከ 800 ሺሕ የሚደርሱ ሰዎች የጉዞ እቅድ እንደሚስተጓጎልም አስታውቋል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞችም የሀዲዱ ጥገና ላይ ተሰማርተዋል፡፡
የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋብሪዬል አታል ፖሊስና የደህንነት አገልግሎት ወንጀለኞቹን ለማግኘትና ለመቅጣት በትጋት እየሰሩ መሆኑን ገልጿል፡፡
የጥቃቱን ምንጭ በመመርመር ላይ ያሉ አካላት በምርመራቸው ተቀጣጣይ ነገሮች በባቡር ጣቢያዎቹ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡ ነገር ግን ከጥቃቱ ጀርባ ማን እንዳለ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም ብለዋል፡፡
የዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት ምንም ስጋት እንደሌላቸውና በፈረንሳይ ባለስልጣናት ሙሉ እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ፈረንሳይ ከቀናት በፊት ለጥንቃቄ አትሎቶችን፣ አሰልጣኞችን፣ ጋዜጠኞችና በጎ ፈቃደኞችን ጨምሮ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ከውድድሩ አስቀድማ ፈትሻ አስገብታለች፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 4 ሺሕ 360 ሰዎች እንዳይገቡ ተከልክለዋል፡፡ 880 የሚሆኑት ደግሞ በውጭ ጣልቃገብነት ተጠርጥረው ጨዋታውን መታደም እንደማይችሉ ተነግሯቸዋል፡፡
የፓሪስ ኦሊምፒክ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ዛሬ ምሽት 12 ሰዓት ተኩል ይደረጋል፡፡ በኦሊምፒክ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜም ከስታዲየም ውጪ በውሃ ላይ ስነስርአቱ ይካሄዳል፡፡ 300 ሺሕ ሰዎችም ይታደማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡