የፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት በሶማሌ ክልል በድርቅ ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ ማድረግ ጀመረ

የካቲት 7/2014 (ዋልታ) የፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት በሶማሌ ክልል በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ ለተፈናቀሉ ዜጎች ለአንድ ወር በቀን አምስት ቦቴ ውሃ ድጋፍ ማሰራጨት መጀመሩን አስታወቀ፡፡

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ በሶማሌ ክልል በተፈጠረው ድርቅ ሳቢያ ለተፈቀሉ በርካታ ዜጎች የውሃ አቅርቦት መሰራጨት እንዳለበት አንስተዋል፡፡

ፕሬዝዳንቷ በቅርቡ በአካባቢው ባደረጉት ጉብኝትም በቀብሪ በያ የሚገኙ ተፈናቃዮች በተለይም የሴቶች የውሃ እጥረት አሳሳቢ መሆኑን እንደገለጹላቸው አስታውሰዋል፡፡

ለዚህ ጥያቄያቸው ምላሽም ጽሕፈት ቤታቸው በአካባቢው በድርቅ ሳቢያ ለተፈናቀሉ ዜጎች ለአንድ ወር በቀን አምስት ቦቴ ውሃ ድጋፍ ማሰራጨት መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡

ችግሩን በፍጥነት ለመቆጣጠርም ለዘላቂ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ከክልሉ መንግሥት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ነው የገለጹት፡፡