የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳታፊነት የመጠላለፍ ፖለቲካን ያስቀራል ሲሉ አቶ አባዱላ ገመዳ ገለጹ

ተፎካካሪ ፓርቲዎች በየደረጃው ባሉ የመንግሥት ኃላፊነት ቦታዎች ውስጥ እንዲሳተፉ መደረጉ ያለፈውን የመጠላለፍ ፖለቲካ ምዕራፍን ዘግቶ አዲስ የመተባበር መንፈስ እንደሚፈጥር ፖለቲከኛ አባዱላ ገመዳ ገለጹ።
የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት በየደረጃው ባሉ የመንግሥት ኃላፊነት ቦታዎች ውስጥ እንዲሳተፉ መደረጉ ያለፈውን የመጠላለፍ ፖለቲካ ምዕራፍ ዘግቶ ወደ አዲስ የመተባበር ምዕራፍ የሚያሸጋግር የፖለቲካ ባህል የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
ብዙ ዘመናችን የተቃጠለው አዲስ ነገር በመፍጠር፣ ወደፊት በመራመድና በመተጋገዝ ሳይሆን በተለያዩ ሰበቦች አንዱ ሌላውን እያሳደደ ነው ያሉት አቶ አባዱላ ገመዳ፣ ይህን አልፈን ወደ ትብብር ስንመጣ ለመጠላለፍ የምናጠፋውን ጊዜ፣ መዋዕለ ንዋይና ዕውቀት አገራችንን ወደፊት ለማሸጋገር እንድናውለው ያደርጋል ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።
ሂደቱ ቀደም ብለን ከለመድነውና ከምናውቀው ወጣ ባለ መንገድ የሀሳብ ልዩነት አገርን ከማገልገልና አገርን ወደፊት ከማራመድ ተነጥሎ መታየት እንደሌለበት ያየንበት ነው ያሉት አቶ አባዱላ፣ በመሰባሰብና በመተባበር እንጂ በመለያየት አገርን ወደፊት ማራመድ እንደማይቻል በግልጽ የታየበት መሆኑንም ጠቁመዋል።
እንደ አቶ አባዱላ ገለጻ፣ በአገር ደረጃ ቀርቶ በቤተሰብ ውስጥም የሀሳብ ልዩነት የተለመደ ነው፤ ልምዳችን አገርን በማስቀደም መፎካከርና የሀሳብ ልዕልና ያለው ወደፊት እንዲመጣ መንገድ መክፈት ሳይሆን በጠላትነት በመፈረጅ አንዱ ሌላውን እስካልጣለ፣ እስካላፈረሰና እስካላጠፋ ድረስ የማይቀጥልበት የፖለቲካ ባህል ነበር።