የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙኃንና መንግሥታት ከአፍራሽ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ጠየቀ

ኅዳር 9/2014 (ዋልታ) የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙኃን፣ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት፣ መንግሥታትና ግለሰቦች የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በማዛባት እየተበተነች አስመስለው የሚያቀርቧቸው ዘገባዎች የፕሮፖጋንዳ ጦርነት አካል መሆናቸውን በመጥቀስ እንዲታረሙ አሳሰበ፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ሕዝቡ ተደራጅቶ አገሩን  ከውስጥና ከውጭ ጠላት እንዲጠብቅ ያሳሰበ ሲሆን በተለያዩ ቦታዎች አሸባሪው ኃይል ከመኖሪያ ቄዬያቸው ያፈናቀላቸውን ንጹሀን ዜጎች መንግሥትና ሕብረተሰቡ በጋራ በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጥሪ አቅርቧል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ ለዓለም ዐቀፍ  መገናኛ ብዙኃን  በሸራተን አዲስ ሆቴል መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ታሪክ ባለቤትና የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ቀንዲል መሆኗን የጠቀሰው የጋራ ምክር ቤቱ ዴሞክራሲያዊና የሰለጠነ የፖለቲካ ስርዓት እንዲፈጠር ለረጅም ጊዜ ሙከራዎችን ስታደርግ እንደነበርና ለዚህም በርካታ የህይወት መስዋትነት መከፈሉን አስታውሷል፡፡

ምክር ቤቱ በሰጠው መግለጫ አሁን ለተፈጠረው ጦርነት መንስኤው አሻባሪው የሕወሓት ቡድን መሆኑን ጠቅሶ ከ20 ዓመት በላይ ተቀማጭነቱን ትግራይ ላይ ባደረገው የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ የፈጸመው ጥቃት የክህደቱ ጥግ ማሳያ እንደሆነ አለም ሊገነዘብ ይገባል ብሏል፡፡

1 ዓመት ያስቆጠረው ይህ ጦርነት እየሰፋ በመምጣቱና በተለይም በአማራና በአፋር ክልሎች ሕዝብ ላይ ከፍተኛ የሆነ ውድመት ማስከተሉንና ለዚህም ምክንያቱ የአሸባሪው ሕወሓት የአገር አፍራሽነት ጦረኝነት እንደሆነ መግለጫው አውስቷል፡፡

ከሕጋዊ መንግሥት ውጭ የትኛውንም የአሻጉሊት መንግሥት በሕዝብ ላይ የመጫን ሐሳብ የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍጹም እንደማይቀበልና የጋራ ምክር ቤቱም በጽኑ እንደሚያወግዘው አሳውቋል፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጠቀሜታ አድንቀው፣ አዋጁ ተግባራዊ ሲደረግ ንጹሃን ዜጎችን እንዳይጎዳ በጥንቃቄ እንዲፈጸምና መንግሥት የጀመረውን በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ ችግሮችን ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥልበትም   ጠይቋል፡፡