የ173 ሚሊዮን ብር ውድመት የደረሰበት የኮምቦልቻ ቅርንጫፍ ጉምሩክ ወደ ሥራ ተመለሰ

ጥር 28/2014 (ዋልታ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኮምቦልቻ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በአሸባሪው ሕወሓት የደረሰበትን ውድመት በአካል ተገኝቶ ምልከታ አድርጓል፡፡
በዚህም የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱን ኃላፊዎች ሰራተኛው ወደ ሥራ እንዲመለስ የሥነ-ልቦና ስልጠናዎችን በመስጠትና ሌሎች እንቅስቃሴዎችን እያረጉ መሆኑን ተመልክተዋል፡፡
ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱን ዳግም ወደ ሥራ ለማስገባት ከሚደረገው ጥረት ባሻገር አሰራሩን አዘምኖ ከወረቀት የፀዳ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት የሚበረታታ መሆኑን የገለፁት የቋሚ ኮሚቴው አባላት በተቋሙ ውስጥ ግንባታው የተቋረጠው ህንፃ ግንባታው እንዲቀጥል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ወራሪ ቡድኑ በተቋሙ 173 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የተቋሙን ንብረቶች እንዲሁም በኮምቦልቻ ደረቅ ወደብ ሌላ 252 ኮንቴነሮች መዘረፋቸውን የጽ/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ ሰማን ዳውድ ጠቁመዋል፡፡
ሆኖም በአሁኑ ሰዓት የተለያዩ ንብረቶችን ጠግኖ ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተደረገ ስለመሆኑ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡