የ6ኛው ብሔራዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ሚያዝያ 14/2013 (ዋልታ) – የ6ኛው ብሔራዊ ምርጫ ሂደት ነጻ፣ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ እንዲሆን በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በፊት ከክልል አመራሮች እና ከምርጫ ቦርድ ጋር ባካሄዱት ስብሰባ፣ ቀሪ የምርጫ ጣቢያዎች እንዲከፈቱ እና ያልተጠናቀቁ ጉዳዮች እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ መቀመጡን አስታውቀዋል፡፡

በዛሬው ዕለት በምርጫው ሂደት አስካሁን የነበሩትን ክንውኖች በሚመለከት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከክልል ርእሳነ መስተዳድሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።

ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ አንዱ ማሳያ ሲሆን፣ ልዩነቶች በጥይት ሳይሆን በምርጫ ካርድ አማካኝነት የሚፈቱበት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ጠቁመዋል፡፡

በምርጫ ሂደት ዜጎች የተማመኑበትን በሙሉ ልብ ለመምረጥ እና ዴሞክራሲያዊ ሂደትን ለመገንባት ንቁ ተሳትፎ የማድረግ ዕድል ያገኛሉ ነው ያሉት፡፡

መጪው ምርጫ ኢትዮጵያን ወደ ፊት የሚያስፈነጥር እንደ መሆኑ መጠን በጋራ የዜግነት ግዴታችንን መወጣት ያስፈልገናል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡