ዩኒሴፍ ለድርቅ ተጎጂዎች የሃብት የማሰባሰብ ሥራ እሰራለው አለ

ሚያዝያ 20/2014 (ዋልታ) ዩኒሴፍ በአፍሪካ ቀንድ በተከሰተው ድርቅ ተጎጂዎች አፋጣኝ ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ የሚያስችል ሃብት የማሰባሰብ ሥራ እንደሚሰራ አስታወቀ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ራስልን ጋር ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ ውስጥ እያደረጋቸው ስላሉ የልማት እና የሰብአዊ ድጋፍ ሥራዎች አጠናክሮ መቀጠል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተው ድርቅ በኢትዮጵያ ውስጥ በሰዎች እና እንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ የገለፁ ሲሆን መንግሥት አደጋውን ለመከላከል መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በጦርነት የወደሙ መሰረተልማቶችን መልሶ ለመገንባት እና ለድርቅ ተጎጂዎች አስቸኳይ የሰብአዊ አርዳታን ተደራሽ ለማድረግ እንደዩኒሴፍ ያሉ የልማት አጋሮች ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን በበኩላቸው መንግሥት ትኩረት በሚሰጣቸው መስኮች ላይ ዩኒሴፍ ሁለንተናዊ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ አመላክቷል።
በቀጠናው የተከሰተው ድርቅ በሌሎች ዓለም ክፍሎች ባሉ ግጭቶች ተሸፋፍኖ ትኩረት እንዳያጣ በማሰብ በአፍሪካ ቀንድ ጉብኝት እያደረጉ እንደሚገኙ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሯ ዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ ለድርቁ ተገቢ ትኩረት እንዲሰጥ በማድረግ ለተጎጂዎች አፋጣኝ ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ የሚያስችል ሃብት የማሰባሰብ ሥራ እንደሚሰራ ገልፀዋል።