ዩኒቨርሲቲው በቀጣዩ ዓመት የጅቡቲ ፖሊሶችን ተቀብሎ ማስተማር ሊጀምር ነው

ግንቦት 29/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በቀጣዩ ዓመት የጅቡቲ ፖሊሶችን ተቀብሎ በሁለተኛ ዲግሪ ማስተማር ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከሀገሪቷ ሁሉም አካባቢዎች የፖሊስ አባላትንና መኮንኖችን በመቀበል በተለያዩ የትምህርት መስኮች አስተምሮ በማስመረቅ ዘመናትን የተሻገረ ስራ በመስራት ይታወቃል።

በቀጣዩ ዓመት ደግሞ የጅቡቲ ፖሊሶችን ተቀብሎ በሁለተኛ ዲግሪ ማስተማር ሊጀምር መሆኑን የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ተሻለ ተሾመ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ደህንነት ለማስፈን ከአገራት አቻ ተቋማት ጋር አብሮ ለመስራት የተለያዩ ስምምነቶችን እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከስምምነቶቹ አንዱ አገራቱ ያላቸውን የፖሊስ ኃይል በዕውቀትና በቴክኖሎጂ ማዘመን አንዱ መሆኑን አመልክተው፤ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የጅቡቲ ፖሊሶችን ተቀብሎ የሚያስተምረውም በዚሁ የትብብር ማዕቀፍ መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም በሚቀጥለው ዓመት የጎረቤት አገር ጅቡቲ ፖሊሶችን ተቀብሎ በሰላምና ደህንነት የትምህርት መስክ በሁለተኛ ድግሪ ለማስተማር ተዘጋጅቷል ብለዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ከሶማሌ ላንድ፣ ደቡብ ሱዳን እና ከሩዋንዳ የፖሊስ አባላትን ተቀብሎ ማስተማሩን ጠቁመው፤ ይህም በቀጣናው ያለውን የፖሊስ ኃይል ለማጠናከር ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ነው የተናገሩት።