ዩኒቨርሲቲው የሚሰጣቸው ትምህርቶች ከኢንዱስትሪዎችና ከገበያ ፍላጎት ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

ሰኔ 21/2013 (ዋልታ) – የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የሚሰጣቸው የትምህርት ዓይነቶች ከኢንዱስትሪዎችና አጠቃላይ የገበያ ፍላጎት ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ ሥርዓተ ትምህርቱን እየከለሰ መሆኑን አስታወቀ።

ከዚህ በኋላ ለግለሰብ ፍላጎት ሳይሆን ገበያውን ታሳቢ ያደረጉ የትምህርት ክፍሎች ብቻ እየተከፈቱና አላስፈላጊ መሆናቸው የታመነባቸው እየተዘጉ አምራች ትውልድን የማፍራቱ ሥራ ይከወናል ሲሉ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ታከለ ታደሰ (ፕ/ር) ተናግረዋል።

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የአፕላይድ ዩኒቨርሲቲዎችን ሥርዓተ ትምህርት እንደ አዲስ መቅረፅ ወይም ማሻሻል የሚል ሃሳብን ያነገበ ውይይት እየተካሄደ ነው።

በውይይት መድረኩ የተገኙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) የከፍተኛ ትምህርት ሥርዓት ዓይነተ ብዙ ችግሮች ያሉበት እንደነበር ገልጸዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጥራት፣ ተደራሽነት፣ የትምህርት ተገቢነትና ፍትሓዊነት ይነሳባቸው የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

ከእነዚህ ማሻሻያዎች ውስጥ ደግሞ ተቋማቱን በተልዕኮና በትኩረት መስኮች ለይቶ ማደራጀት መቻሉ አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ተቋማቱ በዘርፍ ከመደራጀት ባሻገር በተመደቡበት መስክ ብቁና ተወዳዳሪነታቸውን እየፈተሹ፤ የሚሰሩት ምርምርም ምን ያክል ችግር ፈቺና ተተግባሪ ነው የሚለውን እያጤኑ እንዲጓዙ አሳስበዋል።

ከዚህ በኋላ አዲስ የትምህርት መርሃ ግብር ሲከፈት ቀድሞ የማኅበረሰቡን ፍላጎት የማጥናትና የማወያየት፣ የዓለም ዐቀፉን የትምህርት ሥርዓት ደረጃም የለካ መሆኑን የማረጋገጥ ጉዳይ ግዴታ ነው ሲሉም ሚኒስትር ዴኤታው አሳውቀዋል።

ተማሪዎች ከተመረቁ በኋላ ምን እየሰሩ ነው የሚለውም ጥናት እየተደረገበት የትምህርት መርሃ ግብሮች ገበያ ተኮርነት በተግባር የሚለካበት አሰራርን መንግሥት እንደሚከተልም አመላክተዋል፡፡

(በስንታየሁ አባተ)