ዩኤስኤይድ ለኢትዮጵያ 313 ሚሊዮን ዶላር የሰብኣዊ ድጋፍ አደረገ

ሚያዝያ 14/2014 (ዋልታ) የአሜሪካ ዓለም ዐቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩ ኤስ ኤይ ድ) ለኢትዮጵያ ተጨማሪ 313 ሚሊዮን ዶላር የሰብኣዊ ድጋፍ ማድረጉን ገለፀ፡፡
ድጋፉ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተከሰተው ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው የአፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልል ዜጎች የሚውል ድጋፍ መሆኑ ተጠቅሷል።
በክልሎቹ የሚገኙ 7 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የምግብና የመጠጥ አቅርቦት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ድርጅቱ አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ ከጥር ወር ጀምሮ በአማራና በአፋር ክልሎች ብቻ ከ4 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የምግብ ድጋፍ ማድረጉን አንስቷል፡፡
የፌዴራል መንግሥትና የአካባቢው ባለሥልጣናት የሰብኣዊ እርዳታ በየብስ ትራንስፖርት ወደ ትግራይ እንዲገባ ባደረጉት ውሳኔ ድርጅቱ ከ100 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የምግብና ለህጻናት የሚሆኑ የአልሚ ምግቦች እንዲደርስ ማድረጉን ገልጿል፡፡