ያለአገር አልኖርም ያሉት እናት ቤታቸውን 2 ሚሊዮን ብር በመሸጥ ለመከላከያ ሰራዊት አበረከቱ

ኅዳር 17/2014 (ዋልታ) የእኔ በድሎትና ተከብሬ የመኖር ምስጢር አገሬ ናት ያሉት እናት ቦጋለች ከበደ የመኖሪያ ቤታቸውን 2 ሚሊዮን ብር በመሸጥ ለአገር መከላከያ ሰራዊት አበረከቱ፡፡
ኢትዮጵያ እንድትቀጥል የሚቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ በማለት ነው ቤታቸውን ሸጠው ለመከላከያ ሰራዊቱ ያበረከቱት፡፡
አገሬ ለኔ መጦሪያዬ ስሞት ደግሞ መቀበሪያዬ ናት ያሉት እናት ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ድል እስክታደርግና አገሬ በኅልውናዋና ሉኣላዊነቷ እንድትቀጥል ድጋፌን አላቋርጥም ብለዋል።
በተመሳሳይ ዜና የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ለአገር መከላከያ ሰራዊት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የአይነት ድጋፍ አድርጓል።
ድጋፉን ያስረከቡት የኮርፖሬሽኑ ምክትል ሥራ አስፈፃሚ ኃይለብርሃን ዜና ጦርነቱ በግንባር ብቻ የሚደረግ ሳይሆን በምጣኔሃብቱም በርካታ ጦርነቶች ተደቅነውብናል ያሉት ሲሆን ምጣኔሃብቱን ለመደገፍ ኮርፖሬሽኑ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በዙፋን አምባቸው