ደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ በአገራዊ ምክክሩ ዙሪያ የምሁራን መድረክ እንደሚያዘጋጅ ገለጸ

መጋቢት 21/2014 (ዋልታ) በአገራዊ ምክክር ጉዳይ ላይ ሁሉንም አካላት ግንዛቤ ሊያስጨብጥ የሚያስችል የምሁራን ምክክር መድረክ በቅርቡ እንደሚያዘጋጅ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ለታ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በአገር ዐቀፍ ደረጃ በሚካሄደው አገራዊ ምክክር ዙሪያ ለሁሉም አካላት ግንዛቤ ሊያስጨብጥ የሚያስችል የምሁራን መድረክ ለማዘጋጀት እየሠራ ነው።

መድረኩ ምሁራን ካላቸው ዕውቀት በመነሳት የአገራዊ ምክክሩን ፋይዳ ኅብረተሰቡ እንዲገነዘበው ማድረግን ያለመ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ምሁራን በአገራዊ ምክክሩ አስፈላጊነት መተማመን ከፈጠሩ እነሱ ያመኑበትን ጉዳይ ለሌሎች ለማስረዳትና አገራዊ ምክክሩን ያማከሉ ጥናቶችን በማካሄድ እንዲሁም ጠቃሚ ሐሳቦችን በማመንጨት ለስኬታማነቱ የድርሻቸውን እንዲጫወቱ የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።

ከምሁራኑ መድረክም ኅብረተሰቡ የአገራዊ ምክክር ምንነትንና አስፈላጊነትን በመረዳት በባለቤትነት ስሜት እንዲሳተፍ ያደርጋል ያሉት ፕሬዝዳንቱ አገራዊ ምክክሩ በምሁራን ምክክር መታገዙ ሕዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው አስገንዝበዋል።

ዩኒቨርሲቲው አገራዊ ምክክሩን ስኬታማ ለማድረግ ካለው ሀብት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጸው ከሁሉም በላይ ምሁራንና ሚዲያዎች በገለልተኝነት ሙያዊ ግዴታቸውን መወጣት ምክክሩን የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ምሁራንና ሚዲያዎች አገራዊ ምክክሩን ሊያደናቅፉ ከሚያስችሉ ድርጊቶች በመታቀብና በመጠንቀቅ ገለልተኛ ሆነው መዘገብ አለባቸው ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡