ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚደረግ ጥረት ሁሉ በአፍሪካ ላይ እንደተቃጣ ስጋት ይቆጠራል አለች

ኅዳር 11/2014 (ዋልታ) የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ የሆነችው ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚደረግ ጥረት ሁሉ በአጠቃላይ በአፍሪካ ላይ እንደተቃጣ ስጋት የሚቆጠር መሆኑን ደቡብ ሱዳን ገለፀች።
በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማህዲ አዲስ ከተሾሙት የደቡብ ሱዳን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስተር ማሃሙድ ሰለሞን አጎክ ጋር ተወያይተዋል።
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያዊያን ለደቡብ ሱዳን ነጻነት የሕይወት መሰዋዕት መክፈላቸውን በማስታወስ፣ ይህንንም እራሳቸው በትግል ወቅት በተግባር ያረጋገጡት ሃቅ መሆኑን መስክረዋል።
ሚኒስትሩ አያየዘውም ከዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ የግጭት መናሃሪያ ሆና ማየት አንደማይሹ ገልጸዋል።
አምባሳደር ነቢል ሕወሓት እየፈጸመ ያለውን እኩይ ተግባር ለመመከት መንግሥት እያደረገ ያለውን ጥረት ለሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም የምዕራባዊያን ፅንፈኛ መገናኛ ብዙኃን ተቋማት የሃሰት መረጃን በማሰጨት የመንግሥትን ቅቡልነት አጠያያቂ ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የመረጃ ተቋማቱ በኢትዮጵያ ያሉ የተለያዩ አገራትና ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑን በመጥቀስ ላይ መሆናቸውን በማስታወስ፣ ይህ ከእውነት የራቀ መሆኑንና ኢትዮጵያ የዲፕሎማቶችን መብትና ጥቅም የሚያስጠብቀውን የቬይና ስምምነት በጥብቅ እንደምታከብር ገልጸዋል።
መረጃው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ነው።