ደጀን ወደ ሆነው ሕዝባችን ስንገባ የተደረገልን አቀባበል ሰራዊቱን ያስደመመ ነው- ኮሎኔል ሻምበል በየነ

ኮሎኔል ሻምበል በየነ

ሐምሌ 01/2013 (ዋልታ) – ደጀን ወደ ሆነው ህዝባችን ስንገባ የተደረገልን ደማቅ አቀባበል ሰራዊቱን ያስደመመ እንደነበር የ23ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ባለከዘራው ኮሎኔል ሻምበል በየነ አስታወቁ።

ጁንታው ገደልን ማረክን እያለ ማሳሳት የኖረበት ባህሪው መሆኑን የጠቆሙት ኮሎኔል ሻምበል በየነ፣ በአማራ ክልል ዋግኽምራ አስተዳደር ዞን አበርገሌ ወረዳ ስንደርስ በህዝቡ የተደረገልን አቀባበል ደማቅ እና ሰራዊቱ የህዝብ ሰራዊት መሆኑን በተጨባጭ ያሳየ ነው ብለዋል።

እኔ በግሌ የህዝቡን አቀባበል የምጠብቀው ቢሆንም፤ በሰራዊቱ ዘንድ በዚህ ደረጃ አቀባበል ይደረጋል ብሎ አልጠበቀም ነበር ያሉት ኮሎኑሉ፣ በያለፍንባቸው አካባቢዎች ሕዝቡ ለሰራዊቱ ያለውን ፍቅር የገለጸበት መንገድ ከፍ ያለ የሞራል ስንቅ እንደሚሆን ገልጸዋል።

ህዝቡ ለሰራዊቱ የሚበላም የሚጠጣም በማቅረብ ለሰራዊቱ ያለውን ድጋፍ በተግባር አሳይቷል፤ በተለያየ ደረጃ የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል አቀባበሉ የተለየ ነው፤ ይህ በጣም ተአምር ነው፤ በእዚህ ምክንያት መከላከያ ያቀረበልንን ምግብ መጠቀም አልቻልንም ሲሉም አመልክተዋል።

ጁንታው የውሸት ፕሮፖጋንዳን እንደ አንድ የውጊያ ስልት በማድረግ ይጠቀማል፤ በዚህም ያልማረከውን ማረኩ፤ ያልገደለውን ገደልኩ ማለቱ አዲስ አይደለም ብለዋል፡፡ ‹‹ባለከዘራው ኮሎኔልን ከበነዋል፣ ማርከነዋል፣ ገድለነዋል›› ያሉትም የዚሁ ባህሪው መገለጫ ነው ብለዋል።

እኔን ማረኩ ገደልኩ ሲል የነበረው እኔ ከሌላው አመራር የተለየሁ ሆኜ ሳይሆን በሕዝቡና በሰራዊቱ ያለኝን ተቀባይነት ግምት ውስጥ በማስገባት ላሰለፋቸው ታጣቂዎች የተዳከመ የሞራል አቅም ለመገንባት እንደሆነ አመልክተዋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል፡፡