ዲያስፖራው የወደሙ የትምህርት ተቋማትን ለመገንባት እንዲያግዝ ጥሪ ቀረበ

ጥር 30/2014 (ዋልታ) በስዊዘርላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የዲያስፖራ አባላት በአፋርና በአማራ ክልል የወደሙ የትምህርት ተቋማትን ለመገንባት አበርክቶ እንዲኖራቸው የሚያስችል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ማዘጋጀት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የበይነ መረብ ውይይት ተካሄደ፡፡

በስዊዘርላንድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ዘነበ ከበደ የዲያስፖራ አባላቱ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት በቀጣይ በስዊዘርላንድ በሚካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል::

አምባሳደር ዘነበ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለመርዳት ያሳዩት ተሳትፎ እጅግ የሚበረታታ መሆኑን በመግለጽ ምስጋናቸውንም አቅርበዋል፡፡

ወደ አገር ቤት የመግባት ጥሪ መሰረት በርካታ የዲያስፖራ አባላት መሳተፋቸው ጠላቶቻችንን ያስደነገጠና ዕቅዳቸውን ያካሸፈ፣ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖቻችንን ደግሞ ተስፋና ሞራል የገነባ ምን ጊዜም የወገን ደራሽ ወገን መሆኑን ያረጋገጠና የሚያኮራ መሆኑን አምባሳደር ዘነበ አንስተዋል::

በውይይቱ የአፋር እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮዎች ኃላፊዎች በሁለቱ ክልሎች በአሸባሪው ትሕነግ ወረራ የደረሱ ጉዳቶችን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።