ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025ን እውን ለማድረግ የመንግስት ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው ተገለጸ

ነሐሴ 27/2015 (አዲስ ዋልታ) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025ን እውን ለማድረግ ሁሉም የመንግስት ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አሳሰበ።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የአጋማሽ ጊዜ የስራ አፈፃፀም የማረጋገጫ መድረክ ማጠቃለያ የተካሄደ ሲሆን ከ50 በላይ የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ተሳትፈውበታል፡፡

በመደረኩ በስትራቴጂው እንዲተገበሩ የተቀመጡ ስራዎች የደረሱበትን ደረጃ መረጃ የመሰብሰብ እና የማረጋገጥ ስራ ተሰርቷልም ነው የተባለው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025ን እውን ለማድረግ ሁሉም የመንግስት ተቋማት እና የግሉ ዘርፍ በትብብር እና በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

በሁሉም ስራዎች ፈጣን የመረጃ ፍሰትና መናበብ ሊኖር ይገባል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ በቀጣይ የተጠቃለለና የተረጋገጠ መረጃ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ አመልክተዋል።

ግብርና፣ ቱሪዝም፣ በዓለም አቀፍ የእሴት ሰንሰለት ውስጥ የሚገቡ አምራች እንዱስትሪዎች፣ እና በኢንፎርሜሽን እና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ አስቻይነት የሚተገብሩ አገልግሎቶች በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ቅድሚያ የሰጣቸው ዘሮፎች መሆናቸውም ተጠቁሟል።

መሰረተ ልማት መገንባት፣ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር፣ ዲጂታል መተግበሪያዎች እና የዲዲታል ስነ ምህዳር መፍጠር የስትራቴጂው መሰሶዎች ሲሆኑ እነዚህን ለመዘርጋት ተቋማት ሀብትን በመቆጠብ እና በመጋራት ሊሰሩ ይገባል መባሉን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።