ዲፕሎማሲ -ኢትዮጵያ የታጠቀችው ሰላማዊ ሚሳኤል

የህዳሴ ግድቡን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት

ዲፕሎማሲ – ኢትዮጵያ የታጠቀችው ሰላማዊ ሚሳኤል
—————————————-
በነስረዲን ኑሩ

ግብጽ የህዳሴ ግድቡን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ለማስተጓጎል በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ የ22 ሃገራትን ደጅ ጠንታለች፡፡ ሱዳንም በአቅሟ የተቻላትን ስታደርግ ቆይታለች፡፡

ወደ ስልጣን ለመውጣት በአንድ ጀምበር ከ5 ሺህ በላይ ግብጻዊያንን በታህሪር አደባባይ የፈጀው የአልሲሲ አስተዳደር ለቅኝ ግዛት አስተሳሰቡ ደጋፊ አገራትን ከጎኑ ለማሰለፍ ያደረገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ግን ንጹሃን ዜጎችን ፈጅቶ ስልጣን እንደመቆናጠጥ ቀላል አልሆነለትም፡፡

የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሹክሪ ኢትዮጵያ በገዛ ሃብቷ መጠቀም እንዳትችል የሚያደርጉ አስገዳጅ እና አሳሪ ሰነዶች የታጨቁበት ቦርሳቸዉን ሸክፈው ከአሜሪካ ካናዳ፣ ከሲውዘርላንድ ሆላንድ፣ ከአረብ ሊግ እስከ አፍሪካ ህብረት፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እስከ ሩቅ ምስራቅ ብቻ በመላው ዓለም ሲንከራተቱ ያለፉትን ወራት ቢያሳልፍም የተንኮል ተልዕኳቸው ግን ሊሳካላቸው አልቻለም፡፡

ሃገሪቱ አለኝ የምትላቸውን ዲፕሎማቶች፣ በተለያዩ ዓለማት የሚኖሩ ግብጻዊያን አክቲቪሰቶች፣ ታዋቂ ሚዲያዎች፣ ጋዜጠኞች እና የአረብ ብሔርተኞች ለዚህ እኩይ ዓላማ ከማሰለፏም ባሻገር ደም መጣጩ አልሲሲ እራሱ ኢትዮጵያ ስትቀር የምስራቅ አፍሪካ ሃገራትን ማካለላቸው አልቀረም፡፡

ምንም እንኳ የግብፅ ደጅ መጥናት ዓባይን ለብቻዋ ለዘመናት ስትጠቀምበት እንደቆየችው ለመቀጠል ያላትን ህልም እውን ማድረግ ባያስችላትም በኢትዮጵያ ላይ ጫና ማሳደሩ ግን አይካድም።

አሜሪካ እና የዓለም ባንክ የህዳሴው ግድብ ድርድር ላይ በታዛቢነት ስም እንዲገቡ ከማሳመን ጀምሮ በማን አለብኝነት ወደ አደራዳሪነት ራሳቸውን ከፍ ለማድረግ በጣሩበት ደባ ውሰጥም የግብጽ እጅ ረጅም እንደነበረ ኢትዮጵያዊያን በቅርበት የሚያስታውሱት ጉዳይ ነው።

ክብርና ምስጋና ለውድ የኢትዮጵያ ልጆች ይሁንና ኢትዮጵያን ወክለው በህዳሴው ግድብ ድርድር ዙሪያ በየመድረኩ የሚደራደሩ ተደራዳሪዎቻችን የታጠቁትን የእውቀትና የሞራል ልእልና ይሁንና የግብጾች እና የሱዳኖች ጥረት እስካሁን -ኢትዮጵያ የታጠቀችውን ሰላማዊ ሚሳኤል ማስፈታት አልቻለም፡፡

እዚህ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት የድርድር ሂደቱ በፖለቲከኞች ሳይሆን በዘርፉ ባለሙያዎች እንዲመራ ያሳለፈው ውሳኔ ለስኬቱ ቁልፍ እርምጃ መሆኑን መጥቀስ ተገቢ ነው። ያ ባይሆን ኖሮ ዛሬ ላይ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ የተባበሩት መንግስታት ደርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ከአንዴም ሁለቴ ደርሶ አይመለስም ነበር፡፡

ለዚህ ድል መሰረቱ ኢትዮጵያ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የምታካሄደው የዲፖሎማሲ ስራ የሞራል ልዕልናን ከግንዛቤ ያስገባ በመሆኑ እና ሀገሪቱ በመከባበር እና በጋራ ብሄራዊ ጥቅም ላይ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ጋር የመሰረተችው ግንኙነት ዛሬ ላይ ግልጽ ሆኖ በማገልገሉ እና የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ከታችኛው ተደራዳሪ ሀገራት ባለሞያዎች ጋር እ.አ.ዘ.አ 2015 እንዲፈረም ያስቻሉት የመርህ ስምምነት መግለጫን መጥቀስ ተገቢ ይሆናል፡፡

ለዚህም ነው አብዛኛው ግብፅ እና ሱዳን ደጅ የጠኗቸው ሀገራት ጉዳዩን በአፍሪካ ህብረት አማካይነት በተጀመረው የሶስትዮሽ ድርድር ብትጨርሱ መልካም ነው የሚል ምክር ሰጥተው የመለሷቸው።

ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ግብፅ ለተለመደው እኩይ አላማዋ ወደ ቻይና ሄዳ የተሰጣት ምክረ ሃሳብ ነው፡፡

ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በውጭ ዲፕሎማሲ ረገድ በየመድረኩ በኢትዮጵያ የምትደቆሰው ግብፅ የሃገር ውስጥ ጫናው ሲበረታባት እንደ ህመም ማስታገሻ አድርጋ የምታወጣውን የህዳሴው ግድብ ጉዳይ ይዛ ወደ ቻይና አመራች።

ቻይና ሆይ አንቺና ኢትዮጵያ ጥብቅ ወዳጅነት እንዳላችሁ አውቃለሁና እባክሽ ይህን ወዳጅነት ተጠቅመሽ የሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌቱን ከመጀመሯ በፊት አስገዳጅ ውል አስፈርሚልኝ ስትል ትጠይቃለች።

ቻይናም እዚህ ድረስ ለመምጣትሽ ክብር እንሰጣለን። ነገር ግን በህዳሴው ግድብ ጉዳይ ኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዳደርግ የጠየቅሽኝን ለመቀበል ግን አልችልም። ምክንያቱም የናይልን ውሃ ግብፅም፣ ሱዳንም ኢትዮጵያም በፍትሃዊነት መጠቀም አለባቸው የሚል እምነት አለኝ። በአፍሪካ ህብረት አማካይነት የተጀመረው ድርድር ፍቱን መፍትሄ እንደሚያስገኝላችሁ አምናለሁ ትላታለች።

ይህን ምላሽ ከሰጠቻት በኋላ ቻይና ቀጠል አድርጋ ግብፅ ሆይ ይኸን ኢትዮጵያ ላይ ጫና ፍጠሪ የምትይውን ነገር ተይኝ እንጂ ላንቺ የሚጠቅም ምክረ ሃሳብ አለኝ ትላታለች። በከርሰ ምድርሽ የሚገኘውን ጨዋማ ውሃ በማከም ለመስኖ አገልግሎት ማዋል የሚያስችል የካበተ ተሞክሮ አለኝና በደስታ ድጋፍ አረግልሻለሁ ብላ ሸኘቻት።

ግን ምን ያደርጋል ግብጽ ምክረ ሃሳቡን ወደ ተግባር ለመቀየር አልወደደችም፡፡

ግብፅ የስልጣን ዘመኑን ከማራዘም በዘለለ ለዜጎቿ የሚጨነቅ አመራር ቢኖራት ኖሮ የህዳሴ ግድቡን የውሃ ሙሌት ለማስተጓጎል ያፈሰሰችውን ሀብት የዜጎቿን ህይወት ለማቅለል በተጠቀመችበት ነበር፡፡

ዘሬም ቢሆን ግብጽ ለሌላ እኩይ ተልዕኮ መዘጋጀቷ የሚጠበቅ ነው። ምክንያቱም ሀገሪቱ ደካማ ነው ብላ ያሰበችውን ከመጨቆን ወደ ኋላ አትልምና፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ ታሪኳ ነው፡፡ በአማርኛ ግብፅ፣ በእንግሊዘኛ ኢጂፕት፣ በአረብኛው ደግሞ ሚስር የምትባለው ሀገር ፈርኦን የተሰኘ ጨቋኝ አስተዳደር ለዓለም አስተዋውቃለችና፡፡ ይህ እውነታ በቅዱስ መጽሀፍትም ተጽ ፏል፡፡

ዲፕሎማሲያዊ ጥረቷ ያልተሳካ ሲመስላትም ጉልበትን የመጠቀም አማራጭ አለኝ ማለቷም ከዚሁ ታሪካዊ እውነታ የሚመነጭ ሀቅ ነው፡፡ ከሱዳን እና ከሌሎች የአረብ ሀገራት ጋር ወታደራዊ ልምምድ ማድረጋቸው ጉልበትን እንደ አማራች ለመጠቀም ያላቸውን ዝንባለሌ ያሳያል፡፡ በኢትዮጵያ ዙሪያ ካሉ ሀገራት ጋር ወታደራዊ ስምምነት መፈራረም፣ የመሪዋ አብዱል ፈታህ አልሲሲ ከአባይ ውሃ አንዲት ጠብታ ብትጎል ሰማይ ዝቅ ምድር ከፍ ትላለች የሚል አይነት ዛቻም ይህንኑ እውነታ ያጠናክራል፡፡

ፍርሃት ፈሪ ይፈልጋል እንዲሉ በአልሲሲ ዛቻም ሆነ አፍንጫችን ስር በተደረገው ወታደራዊ ትርዕት የተሸበረ መንግስት፣ ወታደር እና የኢትዮጵያ ህዝብ የለም።

ኢትዮጵያ በምትከተለው የውጭ ጉዳይ ፓሊሲዋ ቅድሚያውን ችግሮችን በዲፕሎማሲያዊ ጥረት ለመፍታት ስትጥር ኖራለች፣ ዛሬም ለዲፕሎማሲ ቅድሚያ እየሰጠች በመሆኗ ምርቱን እያጨደች ነው።

ከሰሞኑ ግብፅና ሱዳን ባደረጉት የሞት ሽረት ትግል የህዳሴው ግድብ ጉዳይ በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ጉባኤ አጀንዳ ሆኖ እንዲቀርብ ቢያስችልም ውጤቱ ግን ተመሳሳይ ነው።

በጉዳዩ ላይ የምክር ቤቱ አባል ሀገራት አስተያየታቸውን ሲሰጡ ከቱኒዚያ በስተቀር ሁሉም ለማለት በሚያስችል ደረጃ ኢትዮጵያ ስትሟገትለት ከነበረው ሀቅ ጎን መቆማቸውን አረጋግጠዋል።

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሹክሪ በመድረኩ የተለመደ የአዞ እንባውን እያፈሰሰ ለሰላሳ ሁለት ደቂቃ ያህል ተናገረ።

በንግግሩም ኢትዮጵያ በማን አለብኝነት በግብፅና ሱዳን ህዝቦች ላይ ግፍ ለመስራት አቅዳ እየሰራች መሆኗን ለማሳመን ሞከረ። የፀጥታው ምክር ቤትም በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ላይ ኢትዮጵያ የህልውና አደጋ ደቅናለችና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲያስቆም ሲል ጥሪ አቀረበ።

የውሃ መስናና ኤሌትሪክ ሚኒስቴር ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ በተራቸው እንዲህ ሲሉ መልስ ሰጡ፣ “ዛሬ በዚህ ቦታ ስለ ውሀ ለመነጋገር በመገናኘታችን አዝናለሁ!” ብለው ትልቁ ምክር ቤትን እና መላውን ዓለም በማስተማር ንግግራቸውን ጀመሩ፡፡ ምክር ቤቱን ይህ ጉዳይ በፍፁም እንደማይመለከተው አጽንኦት ሰጥተው አስረዱ፡፡

ቀጥለውም ወደ ዋነኛ አጀንዳ ተመለሱና በለስላሳ እና ጣፋጭ አንደበት እንዲህ ሲሉ ቀጠሉ፡፡

“የህዳሴው ግድብ የእያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ አሻራ የታተመበት ነው!”። “ይህ ግድብ እኮ በኢትዮጵያዊያን ላብ፣ ደም እና እንባ የተገነባ ነው፡፡ ፡ለዚህ ምክር ቤት የማቀርበው አንድ ጥያቄ አለኝ፡ ኢትዮጵያዊያን ከአባይ ውሃ መጠጣት ይችላሉን?” ሲሉ በግድቡ ዙሪያ በኢትዮጵያዊያን ላይ እየደረሰ ያለውን ያልተገባ ጫና ፍንትው አንድርገው አሳዩ።

ጉዳዩን በቴሌቪዥን መስኮት የቀጥታ ስርጭት ሲከታተሉ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ንግግራቸው እምባቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው ሲንሰቀሰቁ በጉባኤው የታደሙት የምክር ቤቱ አባላት በድንጋጤ ስሜት ውስጥ ሆነው ተስተውለዋል።

የሆነው ሆኖ ከላይ በተገለፀው መልኩ የፀጥታው ምክር ቤት ውሎ ጉዳዩ በአፍሪካ ህብረት በተጀመረበት ሁኔታ እንዲጠናቀቅ በመግለጽ ምክር ቤት አስፈላጊውን ድጋፍ ኁሉ እንደሚያደርግና በዚህ ጉዳይ ዳግም ጣልቃ እንደማይገባ ውሳኔ አስተላልፎ ተጠናቀቀ።

በዚህ አጋጣሚ የፀጥታው ምክር ቤት ባዘጋጀው በዚህ መድረክ ላይ ጎረቤታችን ኬኒያን ጨምሮ ሩሲያ እና ቻይና ለነበራቸው የማይናወጥ አቋም የኢትዮጵያ ህዝብ በፍፁም የማይረሳው መሆኑን መግለጽ ተገቢ ነው ብሎ ጸሀፊው ያምናል።

የመጨረሻው አማራጭ ጦርነት ከሆነ ግን በሉአላዊነቱ የሚደራደር ኢትዮጵያዊ ይኖራል ተብሎ አይገመትም፡፡ ካለም እሱ ባንዳ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ የኢትዮጵያዊያንን የጀግንነት ታሪክ ለመናገር ከግብፅ የተሻለ ምስክር የለም።

ግብጽ ላለፉት ሀለት መቶ አመታት ኢትዮጵያን ለ19 ጊዚያት ለማጥቃት ሞክራ አይቀጡ ቅጣት ተቀታ ተመልሳላችና፡፡
እዚህ ላይ ታዋቂው ግብፃዊ ተንታኝ የህዳሴ ግድቡን እሰጥ እገባ ሂደት ተከታትሎ የኢትዮጵያን ድል አድራጊነት የገለፀውን እንደወረደ አቅርቤ ፅሁፌን ልቋጭ።

ለምን እንዋሻለን? ኢትዮጵያ ተናግራ ያልፈፀመች ምን አለ?

የአሜሪካን አደራዳሪነት አልፈልግም አለች ። አሜሪካ ተገዳ ከአደራዳሪነት ወጣች።

የአለም ባንክን አደራዳሪነት አልፈልግም አለች። የአለም ባንክ ተገዶ ከአደራዳሪነት ወጣ።

የአውሮፓ ህብረት ታዛቢ እንጅ አደራዳሪ መሆን የለበትም አለች። አውሮፓ ህብረት ታዛቢ ሆነ።

ተመድ የውሀን ጉዳይ በተመለከተ የመወሰን መብት የለውም አለች ። ተመድም አዎ የለኝም እዛው አፍሪካ ህብረት እንደጀመረ እዛው ይጨርስ አለ።

የመጀመሪያውን ሙሌት እሞላለሁ አለች ! ሞልታ አሳየችን።
ሁለተኛውን ሙሊት ያለ ሁለቱ አገሮች ስምምነት መሙላት አትችይም ተብላ በሱዳንና ግብፅ ሲነገራት ሁለተኛውን ሙሊት ከመፈፀም የሚያግደኝ ምድራዊ ሀይል የለም አለች። ይሄው እየሞላች ነው።
ለምን እንዋሻለን ማን አለ እንደ ኢትዮጵያ የሚናገረውን የሚኖር? ማንም የለም። ሲል ጸሀፊው ትዝብቱን ያጋራል። ከላስ!

ዲፕሎማሲያችን ሚሳኤላችን ማለት ይኼው ነው!