ዳሽን ባንክ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የ5 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ

ነሐሴ 30/2014 (ዋልታ) ዳሽን ባንክ አክሲዮን ማህበር ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የ5 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ፒኤችዲ) ድጋፉን በተረከቡበት ወቅት እንደገለጹት ክልሉ በርካታ ለውጭ ምንዛሬ የሚውሉ የግብርና ምርቶች የሚመረትበት አካባቢ መሆኑንም ገልጸዋል።

አያይዘውም ክልሉ መንግስታዊ ተልዕኮዎችን ለማስፈጸም የአጋሮችን ድጋፍ በመጠየቅ ሀብት የማሰባሰብ ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የድጋፍ ጥሪውን ተከትሎ ዳሽን ባንክ ለክልሉ የ5 ሚሊየን ብር ድጋፍ ያደረገ መሆኑን ገልጸው ባንኩ ያደረገው ድጋፍ ለክልሉ ያለውን አጋርነት የበለጠ የሚያጎላ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ምክትል ርሰ መስተዳድሩ ባንኩ ላደረገው ድጋፍ በክልሉ መንግስት ስም በማመስገን ክልሉ ባንኩ ለሚሰራቸው ስራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

ክልሉ በግብርና ሀብት እንቅስቀሴ የታወቀ መሆኑን ገልጸው ከባንኩ ጋር ለመስራት ዝግጅ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

የዳሽን ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አስፋው ዓለሙ ባንኩ የክልሉን መንግስት ጥሪ ተቀብሎ ድጋፍ ማድረጉ በክልሉ ውስጥ በሚደረጉ የልማት ስራዎች አጋርነታችንን ለመግለፅ ያለመ ነው ብለዋል።

ዳሽን ባንክ በቀጣይም በክልሉ ኢኮኖሚን ማሳደግ በሚችሉ ግብርና ዘርፎች ለመስራት ከክልሉ ጋር ውይይት እንዳደረገ እና የባንኩ ትብብርና አብሮ መስራት እንደሚቀጥል መናገራቸውን የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መረጃ ያሳያል።