ዳሽን ባንክ አጠቃላይ ሀብቱ 117 ነጥብ 14 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታወቀ

ጥቅምት 17/2015 (ዋልታ) ዳሽን ባንክ አጠቃላይ ሀብቱ 117 ነጥብ 14 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታውቋል፡፡

የዳሽን ባንክ አክሲዮን ማህበር 29ኛ መደበኛ ጉባኤውን ያካሄደ ሲሆን የአውሮፓዊያኑ 2021/22 የሂሳብ አመት አፈፃፀምን የተመለከቱ ሪፖርቶች ቀርበው ዉይይት ተደርጎባቸዋል።

የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ ዱላ መኮንን እንደገለፁት ምንም እንኳን ተግዳሮቶች የነበሩ ቢሆንም ባንኩ በ20201/22 የሂሳብ አመት መልካም አፈጻጸም አስመዝግቧል ብለዋል።

በዚህም የባንኩ አጠቃላይ ሀብት 117 ነጥብ 14 ቢሊዮን ብር መድረሱን ይህም ከቀደመው አመት ጋር ሲነፃፀር የ24 በመቶ እድገት ማሳየቱ ነው የተገለጸው፡፡

የባንኩ ባለአክሲዮኖች ድርሻም ወደ 14 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ከፍ ያለ ሲሆን ይህም ከቀደመው አመት ጋር ሲነፃፀር የ42 በመቶ እድገት አሳይቷል ተብሏል።

ባለአክሲዮኖቹ ባለፈው ጉባኤያቸው ተጨማሪ ካፒታል ለማቅረብ መወሰናቸውን ተከትሎ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል መጠንም 6 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተገልጿል።

በብርቱካን መልካሙ