ዳያስፖራው በዲጂታል ዲፕሎማሲ የአገሩን ጥቅም የሚያስከብርበት ሁኔታ ይጠናከራል – ዳያስፖራ ኤጀንሲ

ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት
ሐምሌ 06/2013 (ዋልታ) – ዳያስፖራው በዲጂታል ዲፕሎማሲ የአገሩን ጥቅም የሚያስከብርበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ገለጸ።
አገራት ለሚገጥሟቸው የተለያየ አይነት መልክ ላላቸው ፈተናዎች ዲጂታል ዲፕሎማሲውን ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስን እንደ አንድ መውጫ ድልድይ ሲጠቀሙበት ይስተዋላል።
የዲፕሎማሲ ሥራን በዲጂታል ዘርፍ እንዲታገዝ በማድረግ ዘመኑ ይዞት የመጣውን ዕድል እና መልካም አጋጣሚ መጠቀም እንደሚገባም ብዙዎች ይስማሙበታል።
በተለይም ዳያስፖራውና ዲፕሎማቶች በበይነ መረብ እና በሌሎች ሚዲያዎች አገርና ህዝብን በመወከል ግንኙነቶችን በማድረግ የአገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም የማስጠበቅ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ይታመናል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በዲጂታል ዲፕሎማሲ ላይ በርካታ የቤት ሥራዎችን መሥራት የሚጠበቅባት መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ገልጿል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ለኢዜአ እንዳሉት፤ በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባላቸው አቅም፣ እውቀት እና እድል ሁሉ ለአገራቸው ብሔራዊ ጥቅም መከበር መትጋት ይኖርባቸዋል።
ለአገር ገጽታ ግንባታ እና አገሪቱ በተለያዩ አቅጣጫዎች ያለባት ጫና እንዲቀንስ በማድረግ ረገድ በውጭ የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላትን መጠቀም ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢንተርኔት ተደራሽነት በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደገ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ዜጎች አገር የሰጠቻቸውን ኃላፊነት በብቃት በመወጣት የአገራቸውን ጥቅምና ሉዓላዊነት ማስከበር ላይ የሚሰሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በዲጂታል ዲፕሎማሲው አማካኝነት በአገሪቱ ስላለው ሁኔታ የተዛቡ መረጃዎችን በማጽዳት ትክክለኛ መረጃ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማድረስ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራ መስራት እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል፡፡
“አገራት ዲጂታል ዲፕሎማሲውን በማጎልበት የአገራቸውን ሁለንተናዊ ጥቅም እንዲያስከብሩ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል” ያሉት ወ/ሮ ሰላማዊት፤ የኢትዮጵያም ጥቅም እንዲከበር ዲጂታል ዲፕሎማሲውን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
በተለያዩ አገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ ዲጂታል ዲፕሎማሲውን የማጠናከር ሥራ ይቀጥላልም ነው ያሉት።
በተለይም ዳያስፖራዎች በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገጾች ንቁ ተሳታፊ በመሆን የአገራቸው አምባሳደሮች መሆን ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
በየጊዜው የሶሻል ሚዲያ ንቅናቄ በማድረግ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበርና የገጠሟትን ፈተናዎች እንድታልፍ ለችግሮች መፍትሔ ማበጀት ያስፈልጋልም ብለዋል።
ዲጂታል ዲፕሎማሲ ዘመኑ የሚጠይቀውን ፈጣን መረጃ ለዓለም አገራት በማዳረስ አገራትን በመረጃ በማስተሳሰር ረገድ እያሳደረ ያለው ተጽዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ስዊድን፣ ኒውዝላንድ፣ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ቱርክ፣ ስፔን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ስዊዘርላንድ፣ ጃፓን፣ ሲንጋፖር፣ ኖርዌይና ሩስያ ውጤታማ የዲጂታል ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ አገራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።