ዳያስፖራው ገንዘብ በህጋዊ መንገድ የሚልክበትን ሁኔታ የሚያመቻች ምክክር

ጳጉሜ 02/2013 (ዋልታ) ዳያስፖራው ገንዘቡን ወደ ሀገር ቤት በህጋዊ መንገድ የሚልክበትን ሁኔታ የሚያመቻች የበይነ መረብ ውይይት ከመንግስትና የግል ባንክ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተካሄደ።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት “የዛሬው መድረክ የተዘጋጀው ከወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ በዳያስፖራው ዘንድ እየታየ ያለውን በህጋዊ መንገድ ገንዘብ የመላክ ከፍተኛ ፍላጎት ማርካት የሚችሉ የአጭርና የረዥም ጊዜ ስልቶችን መንደፍ በሚቻልበት መንገድ ላይ ለመወያየት ነው” ብለዋል።

የመንግስትና የግል ባንኮች የስራ ኃላፊዎች በበኩላቸው፣ ከዳያስፖራው ሊገኝ የሚችለውን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከማሳደግ አንጻር ያሉ ተግዳሮቶችንና የመፍትሔ ሃሳቦች ማንሳታቸውን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡

በመፍትሔነት ከቀረቡ ሃሳቦች መካከልም ጥቁር ገበያን የሚያባብሱ አንደር ኢንቮይሲንግና ተገቢ ያልሆነ የገንዘብ ዝውውርን ማሻሻል እንደሚገባ፣ በዘርፉ የተሻለ ተሞክሮ ካላቸው ሀገራት ትምህርት መወሰድ እንዳለበትና ገንዘብ ለመላክ የሚከፈለውን ከፍተኛ ክፍያ ባንኮች የሚጋሩበት ሁኔታን ማየት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

ዘመናዊና አነስተኛ ክፍያ የሚጠይቁ የገንዘብ ማዘዋወሪያ መተግበሪያዎችን መጠቀምና በባንኮች መካከል ከፉክክር ይልቅ የትብብር መንፈስ መዳበር አለበት የሚሉትን አንስተዋል።

የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ፍቃዱ ድጋፌ መንግስት በዘርፉ ያለውን ችግር ተረድቶ ልዩ ልዩ የህግ ማዕቀፎችን ማበጀቱን ገልጸው፣ ከችግሩ ስፋትና ውስብስብነት እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ትብብር ማነስ ጋር በተያያዘ በቀላሉ መፍትሔ ማግኘት እንዳልተቻለ ገልጸዋል።

በጥቁር ገበያና በመደበኛው የባንክ ምንዛሪ መካከል ያለውን ልዩነት በዘላቂነት ማጥበብ እንዲቻል ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።