ዳያስፖራዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ከ5.3 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

የካቲት 25/2014 (ዋልታ) በኖርዌይና አሜሪካ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች በአሸባሪው ሕወሓት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ከ5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ።

“እንቁም ለኢትዮጵያ በኖርዌይ” የተሰኘው ድርጅት 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር፤ በሆስተን ቴክሳስ አሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ደግሞ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ነው ድጋፉ ያደረጉት።

ድጋፉን ለኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ምክትል ኮሚሽነር አይደሩስ ሃሰን አስረክበዋል።

ድጋፉን በአሸባሪው ሕወሓት ቡድን ጉዳት ለደረሰባቸው የአፋርና የአማራ ክልሎችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው አገራዊ ጥረት የበኩላቸውን ለመወጣት ያደረጉት መሆኑን እንቁም ለኢትዮጵያ በኖርዌይ ተወካይ ዶክተር ኃይሉ ከበደ ጠቁመዋል።

በሆስተን ቴክሳስ አሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ተወካይ ፍሬው መኮንን በበኩላቸው በቀጣይም በአሜሪካ ቴክሳስ ግዛት የሚገኙ የዳያስፖራ አባላትን በማስተባበር የሚያደጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኤዜአ ነው።

ምክትል ኮሚሽነር አይደሩስ ሃሰን በበኩላቸው ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም ሁሉም ሊረባረብ ይገባል ብለዋል።