ዳይሬክተር ጄነራሉ ሽብርተኝነትን ለመከላከል ዓለም ዐቀፋዊ ትብብርን እያጠናከርን ነው አሉ

ሰኔ 3/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ የሽብርተኝነት አደጋን ለመከላከል ቀጣናዊና ዓለም ዐቀፋዊ ትብብርን ወደ ላቀ ደረጃ የማሳደግ ተግባር በመከናወን ላይ መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

“ሽብርተኝነትን በመከላከል የጋራ ቤታችን የሆነችውን ኢትዮጵያ በጋራ እንጠብቃለን!” በሚል መሪ ሃሳብ ሀገር ዐቀፍ የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ተመስገን ጥሩነህ ሽብርተኝነት ሀገርና ሕዝብን አደጋ ላይ የሚጥል ዓለም ዐቀፍ ስጋት በመሆኑ የመከላከል ተግባሩ ሁሉንም ይመለከታል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ላይ ሊቃጡ የነበሩ የሽብር ድርጊቶችን በማክሸፍና በመከላከል ሂደት የተሳካ ሥራ መሰራቱንም አስታውሰዋል።

በዚህ ተግባር አጠቃላይ የሕዝቡና የጎረቤት አገራት አቻ ተቋማት የነበራቸውን ሚና አድንቀው ቀጣይነት እንዲኖረውም ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ የሽብርተኝነት አደጋን ለመከላከል ቀጣናዊና ዓለም ዐቀፋዊ ትብብሯን ወደ ላቀ ደረጃ የማሸጋገር ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኗንም ጠቅሰዋል።

ሽብርተኝነት በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ስጋት ሆኖ የቀጠለ የጋራ ችግር በመሆኑ የጋራ መከላከልን ይጠይቃል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በውይይት መድረኩ ወቅታዊ የሽብርተኝነት ስጋቶችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ሰፊ ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል።