ድህነትን ለማጥፋት የእያንዳንዱ ዜጋ ብርቱ ጥረት ወሳኝ ነው – ርዕሰመስተዳድር ይልቃል ከፋለ

ጥቅምት 27/2015 (ዋልታ) ድህነትን ማጥፋት እያንዳንዱ ዜጋ የሚያደርገው ብርቱ ጥረት ወሳኝ ነው ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ፒኤችዲ)ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ፣ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንንና (ፒኤችዲ) ሌሎች የክልሉና የፌዴራል የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በደቡብ ውሎ ዞን ወረኢሉ ወረዳ በክላስተር የለማ ስንዴ ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅትም ድህነት የሚጠፋው እያንዳንዱ ግለስብ በሚያደርገው ብርቱ ጥረት መሆኑን የገለጹት ርዕሰ-መስትዳደሩ በክልሉ በተደረገ ከፍተኛ ርብርብ ከ832 ሺሕ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ እየለማ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የግብርና ዘርፉን ለማዘመን በሚደረገው ጥረትም የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
በወርኢሉ ወረዳ 14 ሺሕ ሄክታር መሬት በስንዴ የለማ ሲሆን ከለማው መሬትም ከ567 ሺሕ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የገለፁት ደግሞ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ሰለሞን አይቸው ናቸው።
በክላስተር ለተካሄደው የስንዴ ልማትም ተሳታፊ አርሶ አደሮች ተገቢው የሙያ እገዛ መደረጉን ጠቅስው፤ አስፈላጊውን ግብዓት በመጠቀምም የተሻለ ለውጥ አሳይቷል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አብዱ ሁሴን በበኩላቸው በዞኑ በዚህ የመከር ወቅት 436 ሺሕ 400 ሄክታር በተለያዩ ስብሎች የለማ ሲሆን ከዚህ ውስጥም 172 ሺሕ 700 ሄክታሩን በስንዴ ስብል ማልማት መቻሉን ተናግረዋል።
ከዚሁ በስንዴ ክላስተር ከለማው መሬትም 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ አመልክተው፤ ከሚገኘው ምርትም ለውጭ ገበያ እንደሚቀርብም አስታውቀዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
በጉብኝቱ የክልል፣ የፌደራል፣የዞንና የወረዳ አመራሮች የተገኙ ሲሆን ቀጣይም በዞኑ በሌሎች ወረዳዎች ጉብኝቱ የሚቀጥል እንደሆነም ታውቋል።