ድርጅቱ ሁለገብ የሕክምና ማዕከል ሊገነባ መሆኑን አስታወቀ

ሚያዝያ 14/2014 (ዋልታ) የኩላሊት ህመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ከመንግሥት በነፃ በተረከበው ቦታ ላይ ሁለገብ የሕክምና ማዕከል ገንብቶ ለኩላሊት ታካሚዎች አገልግሎት ለመስጠት ማቀዱን አስታወቀ።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ሰለሞን አሰፋ እንደገለፁት መንግሥት ለድርጅቱ በነፃ የሰጠው መሬት ላይ ሁለገብ ህንፃ በመገንባት የኩላሊት ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ታቅዷል።
በተረከብነው ቦታ ላይ የኩላሊት እጥበት (ዲያሊሲስ) አገልግሎት ለመስጠት እንዲሁም ለገቢ ማሰባሰቢያ የሚሆን ህንፃ ለመገንባት አቅደናል ብለዋል።
በአጠቃላይም ለህመምተኞች ሁለገብ ድጋፍ መስጠት የሚያስችል ማዕከል ለመገንባት ውጥን ተይዟል ማለታቸውን የኢፕድ ዘገባ አመልክቷል።
የሚገነባው ማዕከል በኢትዮጵያ የሚገኙና በችግር ውስጥ ያሉ በርካታ የኩላሊት ህመምተኞችን ለማገልገል ይረዳል ያሉት ዶክተር ሰለሞን በተገኘው መሬት ላይ ከ17 እስከ 20 ወለል የሚደርስ ህንጻ በአምስት ዓመት ውስጥ ለመገንባት መታቀዱን ገልጸዋል።