ድርጅቱ በሐርቡ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ወገኖች ማዕድ አጋራ

መስከረም 1/2015 (ዋልታ) አጉማስ ኢትዮጵያ የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት በካናዳ ከሚገኙ የበጎ አድራጎት ማኅበራት ጋር በመተባበር በደቡብ ወሎ ዞን ሐርቡ መጠለያ ጣቢያ ለተጠለሉ ወገኖች ማዕድ አጋርቷል።
አሸባሪው ሸኔ በከፈተው ጥቃት ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብና ምሥራቅ ወለጋ አካባቢዎች ተፈናቅለው በሐርቡ መጠለያ ጣቢያ የተጠለሉ ወገኖች ቁጥር 6 ሺሕ መድረሱ ተገልጿል።
እነዚህ ወገኖች አዲስ ዓመትን በተሻለ ድባብ እንዲያሳልፉ በማለም ነው የበ አድራጎት ድርጅቱ የካናዳ መሰል ድርጅቶችን በማስተባበር እና 700 ሺሕ ብር ወጭ በማድረግ ማዕድ ያጋሩት።
ድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አብዱሰላም ሽፋው ማዕድ ማጋራቱ በሽብር ቡድኑ የደረሰባቸውን ሥነ ልቦናዊ ጫና ለመቅረፍና የወገን አለኝታነትን ለማሳየት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ማመላከታቸውንም የአሚኮ ዘገባ አመላክቷል፡፡
የኢትዮ ካናዳ ኔትወርክ ለማኅበራዊ ድጋፍ ተወካይ መቆያ ወንድይራድ በበኩላቸው በዓሉን ከተፈናቃይ ወገኖች ጋር በጋራ ማክበር የተለየ የደስታ ስሜት የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ተፈናቃይ ወገኖችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት እየሠሩ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ተፈናቃይ ወገኖች ለተደረገላቸው መስተንግዶ አመስግነው መንግሥት ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።