ድርጅቱ ባለፉት ስድስት ወራት 19 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ማግኘቱን አስታወቀ

ጥር 17/2015 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ባለፉት ስድስት ወራት 19 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ማግኘቱን አስታወቀ፡፡

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሮባ መገርሳ የ2015 ግማሽ በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀምን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በሰጡት መግለጫ ተቋሙ ባለፉት 6 ወራት 2.2 ሚሊዮን ቶን የኦፕሬሽን አገልግሎት ለመስጠት አቅዶ 2.4 ሚሊዮን ቶን አገልግሎት መስጠቱን ገልጸዋል።

ድርጅቱ ባለፉት ስድስት ወራት 3 ሺሕ 79 ኮንቴነር ወደ ውጪ ታሽጎ መላኩን የገለጹት ዋና ስራ አስፈፃሚው ድርጅቱ 19 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ማግኘቱን አስታውቀዋል፡፡

የድርጅቱ መርከቦች በተለያዩ ዓለም አገራት ወደ 850 ሺሕ ቶን እቃ ማጓጓዛቸውን ገልጸው የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ከመቅረፍ አንፃርም ውጤታማ ስራ መሰራቱም አመላክተዋል።

ተቋሙ ተጨማሪ መርከቦችን የመግዛት እንቅስቃሴ የማድረግ ስራ እንደጀመረ ያስታወቁት ዋና ስራአስፈፃሚው ባለፉት ስድስት ወራት ተቋሙን የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የንግድ መቀዛቀዝ ችግሮች እንዳጋጠመውም ተናግረዋል፡፡

በጅቡቲ የመሰረተ ልማት ተግዳሮች እንዳሉና ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

በሱራፌል መንግስቴ