ሰኔ 26/2013 (ዋልታ) – የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ የሚኒስቴሩን የአቅመ ደካማ ዜጎች ቤት እድሳት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አስጀመሩ::
ሚኒስር መስሪያ ቤቱ በዘንድሮው የክረምት በልደታ ክፍለ ከተማ የሚገኙ የ15 አቅመ ደካማ ዜጎችን ቤት ለማደስ እቅድ መያዙን አስታውቋል።
ዶክተር ሊያ በተገኙበት የእድሳት ስራው የተጀመረ ሲሆን፤ በመርሃ ግብሩም ሚንስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለምፀሀይ ጳውሎስና ሌሎች የሚኒስቴሩ አመራሮች ተሳትፈዋል።
በቤት እድሳት መርሃ ግብሩም በክፍለ ከተማው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃና በህመም ላይ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ተገልጿል።
ዶክተር ሊያ በዚህ ወቅት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ጀምሮ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የበኩሉን ተሳትፎ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከጤና ዘርፍ ስራዎች ባሻገር በችግር ውስጥ ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውንም ተናግረዋል።
ከተከናወኑ የበጎ ፈቃድ ተግባራት መካከል በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ማገዝ፣ የጤና ተቋማትን ለአገልገሎት ምቹ ማድረግና የአረንጓዴ አሻራ ስራዎችን ለአብነት አንስተዋል።
በዘንድሮው ክረምትም ሚኒስቴሩ ከልደታ ክፍለ ከተማ ጋር በመተባበር የአቅመ ደካማ ዜጎችን ቤት ያድሳል ነው ያሉት።
የበጎ ፈቃድ አግልግሎት በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ለሰው ልጆች መንፈሳዊ ደስታ እንደሚሰጥ ገልጸው፤ ሚኒስቴሩ የሚያከናውነውን በጎ ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል።
የልደታ ክፍለ ከተማ ዋና ስራአስፈፃሚ ወይዘሮ ሽታዬ መሀመድ በበኩላቸው ክፍለ ከተማው ከተለያዩ አካላት ጋር በመቀናጀት ችግረኞችን ለመደገፍ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ክፍለ ከተማው ይህንን በጎ ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ የጤና ሚኒስቴር የሚያከናውነው የቤት እድሳት የዚሁ በጎ ስራ አካል በመሆኑ ምስጋና አቅርበዋል።