ጀግኖች ደማቸውን ሰጥተው ያስከበሯትን ሀገር በመስዋዕትነታችን እናስቀጥላለን – የመከላከያ ሰራዊት አባላት

ሰኔ 26/2014 (ዋልታ) ጀግኖች ደማቸውን ሰጥተው ያስከበሯትን ሀገር በመስዋዕትነታችን እናስቀጥላለን ሲሉ በሰሜን ምዕራብ ዕዝ የሚገኙ ሜካናይዝድ እና የእግረኛ ክፍለጦር ሰራዊት አባላት ተናገሩ፡፡
አባላቱ የሀገርን ዳር ድንበር ከዉጭ ወራሪ ኃይልና ከውስጥ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ለመከላከል እና የሚሰጣቸውን ግዳጅ በድል ለመወጣት ሌት ተቀን ዝግጁነት የማረጋገጥ ሥራዎችን እየሰሩ አንደሚገኙ አመላክተዋል፡፡
በክፍለ ጦሩ የሚገኘው የ2ኛ ሬጅመንት አዛዥ ሻለቃ አለምነው ተፈራ እንደተናገሩት ሰራዊቱ ተልዕኮውን እና አላማዉን በሚገባ የሚያውቅ፣ በወታደራዊ ዲሲፒሊን የተገነባ ስለሆነ ማንኛውንም ግዳጅ የሚፈፅመው አሰራሩን እና ደንቡን በመከተል ነው፡፡
የሻለቃው አዛዥ አክለውም ሠራዊቱ ወታደራዊ ሳይንስና ጥበብን በሚገባ እንዲላበስ በስልጠና በማብቃት የሀገሩን ሉአላዊነት ክብር በመስዋትነቱ የሚያስከብር አመራርና አባላት ፈጥረናል ብለዋል፡፡
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመድፈር የሚመጣ ጠላት እና ሰላማችንን ለማወክ የሚሯሯጡ የውስጥ ፀረ-ሰላም ኃይሎችንም ይሁን ተላላኪ ባንዳዎች ለመደምሰስ ሰራዊቱ ከምንጊዜውም በላይ በአስተማማኝ የዝግጁነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ሻለቃ አለምነው ተፈራ ተናግረዋል፡፡
በሜካናይዝድ ክፍለጦር የአየር መቃወሚያ ምክትል አዛዥ ሻለቃ መኳንት ደርብ በበኩላቸው ሰራዊቱ ግዳጁን በአጭር ጊዜ እና በአነስተኛ ኪሳራ እንዲፈፅም የተቀናጀ የሜካናይዝድ ተኩስ ድጋፍ መስጠት የሚያስችል ስልጠና መሰጠቱንም ገልፀዋል።
የሜካናይዝድ አባላቱ ከእግረኛ ክፍለጦር ጋር በመቀናጀት የሀገር ሉአላዊነት እንዳይደፈር ሌት ተቀን ዝናብና ብርዱ ሳይበግራቸው የግዳጅ ቀጠናቸውን እየጠበቁ እንደሚገኙ ተናገረዋል፡፡
ከሰራዊት አባላት መካከል ሃምሳ አለቃ ሲሳይ አበራ እና ምክትል አስር አለቃ አቦነሽ ከበደ በሰጡት አስተያየት ጀግኖች ደማቸውን ሰጥተው ያስከበሯትን እናት ሀገር በእኛ መስዕዋትነት ተከብራ እንድትቀጥል በማንኛወም ጊዜ የሚሰጠንን ግዳጅ በድል ለመወጣት ዝግጁ ነን ማለታቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል።